ሕገ ነሺሊ ወይም የኬጥያውያን ሕግጋትኬጥኛ የተጻፉት የኬጥያውያን መንግሥት ሕገ ፍትሕ ነበር። «ነሺሊ» የሚለው ስም ኬጥያውያን ለራሳቸው የነበራቸው ስያሜ ሲሆን ከመነሻቸው ከተማ ከካነሽ ስም ደረሰ።

ብዙ ቅጂዎች ተገኝተዋል። ብዙዎቹም ቅጂዎች በ1480 ዓክልበ. በንጉሥ ተለፒኑ ዘመን ያህል የተቀነባበሩት ሕጎች እንደ ሆኑ ይታስባል። በተለፒኑ ዐዋጅ መጨረሻ ክፍል ሆን ብሎ ስለ መግደልና ስለ ጥንቆላ የሚቀምሩ ሕግጋት ተሰጡና። በዚህ ጽሁፍ ውስጥ «የቀድሞው ሕግ እንዲህ ነበር» ሲል፣ ከ1480 ዓክልበ. አስቀድሞ የኖሩት ሕጎች ይመሰክራል። ሌሎች ቅጂዎች በ1300 ዓክልበ. አካባቢ የታደሰው ወይም የተሻሸለው ሕገ ፍጥሕ ያላቸው ናቸው። እስከ 1186 ዓክልበ. እስከ ወደቀ ድረስ በኬጥያውያን ግዛት ተግባራዊ ነበሩ።

የኬጥያውያን ሕግጋት

ለማስተካከል

በኬጥኛው ጽሑፍ አንዳንድ ቃላት በባላ ርስት ላይ የነበሩትን ግዴታዎች ይገልጻሉ። ግዴቶቹ ሁሉ ምን ያህል እንደ ነበሩ አናውቅም፤ እንዲህ ተተርጉመዋል፦ «አገልግሎት» (/ሻሓን/)፣ «ቀረጥ» (/ሉዚ/ ) እና «ባለ-ዕጅ ግዴታ» (በሱመርኛ ቃል /ቱኩል/-ግዴታ ማለት «መሣርያ-ግዴታ» ይጻፋል።)

ኬጥያውያን አረመኔ አሕዛብ እንደ መሆናቸው ሁሉ፣ ሕጎቻቸው ስለ ጣዖታት፣ ሥነ ሥርዓቶች፣ አንዳንድ ጨካኝ ቅጣቶች ወዘተ ይጠቀሳሉ። ስለ ዝሙት የነበራቸው አስተያየት በተለይ ከጎረቤታቸው ሕገ ሙሴ ወይም ከአብርሃማዊ እምነቶች አስተያየት ይለያል። ባርነትና የባላባቶችም ነጻ ሥራ አይነተኛ ነበሩ፤ እንዲሁም ግብርናና የብረታብረት ሥራ ለኬጥያውያን አይነተኛ ነበሩ።

ከተለፒኑ ዐዋጅ

ለማስተካከል
  • «...እኔ ተለፒኑ በሐቱሳሽ ጉባኤ ጠራሁ። ከዚህ ሰዓት ጀምሮ፣ በሐቱሳሽ ማንም ሰው የንጉሣዊ ቤተሠብ ልጆችን አይበድላቸው ወይም ጩቤ አይዝባቸው!»
  • « ልዑል አልጋ ወራሹ - በኲር ልጅ ብቻ ንጉሥ ሆኖ ይጫን! በኲር ልዑል ባይኖር፣ ሁለተኛው ወንድ ልጅ ንጉሥ ይሁን። ነገር ግን ማንም ልዑል ወንድ ልጅ ባይኖር፣ የታላቅዋን ሴት ልጅ ባለቤት ወስደው እሱ ንጉሥ ይሁን!»
  • « የግድያም ጉዳይ እንዲሚከተል ነው፡ ማንም ሰው ቢገደል፣ የተገደለው ሰው ወራሽ እንዳለ ሁሉ ይደረግበታል። ይሙት ካለ ይሞታል፤ ይካሥ ካለ ግን ይካሣል። ንጉሡ በውሳኔው ውስጥ አይገባም።»
  • « በሐቱሻ ግዛት ውስጥ ስለሚደረግ ጥንቆላ ጉዳይ፦ እነዚህን ጉዳዮች በመግለጽ ትጉበት። ማንም በንጉሣዊ ቤተሠብ ውስጥ ጥንቆላ ቢሠራ ኖሮ፣ ይዙትና ወደ ንጉሡ ግቢ አስረክቡት። ለማያስረክበው ሰው ግን መጥፎ ይሆናል።»

ክፍል ፩ - 1-100 «ማንም ሰው...»

ለማስተካከል
  • 1፦ ማንም ሰው ወንድን ወይም ሴትን በጸብ ቢገድል፣ ለመቃብር ያምጣውና ከራሱ ቤተሠብ ፈልጎ አራት ወንዶች / ሴቶች በምትክ ይሰጣል።
  • 2፦ ማንም ወንድ ወይም ሴትን ባርያ በጸብ ቢገድል፣ ለመቃብር ያምጣውና ከራሱ ቤተሠብ ፈልጎ ሁለት ወንዶች / ሴቶች በምትክ ይሰጣል።
  • 3፦ ማንም ነጻ የሆነውን ወንድ ወይም ሴት መትቶ በስሕተት ቢገድል፣ ለመቃብር ያምጣውና ከራሱ ቤተሠብ ፈልጎ ሁለት ሰዎች በምትክ ይሰጣል።
  • 4፦ ማንም ባርያ የሆነውን ወንድ ወይም ሴት መትቶ በስሕተት ቢገድል፣ ለመቃብር ያምጣውና ከራሱ ቤተሠብ ፈልጎ አንድ ሰው በምትክ ይሰጣል።
[1300፦ በ§3/4 ፈንታ፣ «ማንም ወንድን መትቶ በስሕተት ቢገድል፣ 160 ሰቀል ብር ይከፍላል። ነጻ ሴት ወይም ሴት ባርያ ብትሆን፣ 80 ሰቀል ብር ይከፍላል።»]
  • 5፦ ማንም ነጋዴውን ቢገድል፣ ከራሱ ቤተሠብ ፈልጎ 100 ሚና [=4000 ሰቀል) ብር ይከፍላል። በሉዊያ ወይም በፓላ አገር ቢሆን፣ 100 ሚና ብር ይከፍልና ደግሞ ለሸቀጡ ይከፍላል። በሐቲ አገር ከሆነ፣ ደግሞም ነጋዴውን ለመቃብር ያምጣል።
[1300፦ ማንም ኬጥያዊውን ነጋዴ በሸቀጡ መሃል ቢገድል፣ [...] ሰቀል ብር ይከፍልና ስለ ሸቀጡ ሦስት እጥፍ ይከፍላል። በሸቀጡ መሃል ሳይሆን ማንም በጸብ ቢገድለው፣ 240 ሰቀል ብር ይከፍላል። በስሕተት ብቻ ቢሆን 80 ሰቀል ብር ይከፍላል።]
  • 6፦ ማንም ሰው ወንድም ሆነ ሴት በሌላው ከተማ ቢገደል፣ ከተገኘበት ርስት ባለቤት ዘንድ የተገደለው ሰው ወራሽ 12,000 ካሬ ሜትር መሬት ለራሱ ይወስዳል።
[1300፦ ነጻ ወንድ በሌላ ሰው ርስት ሞቶ ቢገኝ፣ ባለቤቱ ርስቱን፣ ቤቱንና 60 ሰቀል ብር ይሰጣል። የሞተችው ሴት ብትሆን፣ ባለቤቱ 120 ሰቀል ብር ይሰጣል። የሞተው ሰው በባድማ ቢገኝ፣ በየአቅጣጫው 3 ማይል ይመዝኑና የሞተው ሰው ወራሽ በዚያው ክብ ውስጥ ከሚገኘው መንደር ክፍያውን ይወስዳል። በዚያው ክብ ውስጥ መንደር ባይገኝ፣ ይግባኝ ማለቱን ይተዋል።]
  • 7፦ ማንም ነጻ የሆነውን ሰው ቢያሳውር፣ ወይም ጥርሱን ቢያጥፋ፣ ቀድሞ 40 ሰቀል ብር ይከፍሉ ነበር። አሁን ግን 20 ሰቀል ብር ከቤተሠቡ ፈልጎ ይከፍላል።
  • 8፦ ማንም ባርያ የሆነውን ሰው ቢያሳውር፣ ወይም ጥርሱን ቢያጥፋ፣ 10 ሰቀል ብር ከቤተሠቡ ፈልጎ ይከፍላል።
[1300፦ በ§7/8 ፈንታ፣ «§ ማንም ነጻ የሆነውን ሰው በጸብ ቢያሳውር፣ 40 ሰቀል ብር ይከፍላል፤ በስሕተት ከሆነ 20 ሰቀል ብር ይከፍላል። § ማንም ባርያ የሆነውን ሰው በጸብ ቢያሳውር፣ 20 ሰቀል ብር ይከፍላል፤ በስሕተት ከሆነ 10 ሰቀል ብር ይከፍላል። § ማንም ነጻ የሆንውን ሰው ጥርስ ወይም 2-3 ጥርሶች ቢያጥፋ፣ 12 ሰቀል ብር ይከፍላል። እንዲህ የተጎዳውም ባርያ ቢሆን የጎዳው 6 ሰቀል ብር ይከፍላል።»]
  • 9፦ ማንም ነጻ የሆነውን ሰው ራስ ቢጎዳ፣ ቀድሞ 6 ሰቀል ብር ይከፍሉ ነበር፣ የተጎዳው 3 ሰቀል ብር ወስዶ ለቤተ መንግሥትም 3 ሰቀል ብር ይወስዱ ነበር። አሁን ግን ንጉሡ ስለ ቤተ መንግሥቱ ድርሻ ይቅር ብለዋል፤ ስለዚህ የተጎዳው 3 ሰቀል ብር ብቻ ይወስዳል።
[1300፦ ማንም ነጻ የሆነውን ሰው ራስ ቢጎዳ፣ የተጎዳው 3 ሰቀል ብር ይወስዳል።]
  • 10፦ ማንም ሰውን ቢጎዳ ለጊዜውም አቅሙን ቢያሳጣው፣ ለሕክምናው ያቀርባል። እስኪድን ድረስ ሌላ ሰው በምትኩ ርስቱን እንዲሠራው ያቀርባል። ሲድን 10 ሰቀል ብር ይከፍለዋል፤ ደግሞ ለሐኪሙ 3 ሰቀል ብር ይከፍላል።
[1300፦ ማንም ነጻ የሆነውን ሰው ራስ ቢጎዳ፣ ለሕክምናው ያቀርባል። እስኪድን ድረስ ሌላ ሰው በምትኩ ርስቱን እንዲሠራው ያቀርባል። ሲድን 10 ሰቀል ብር ይከፍለዋል፤ ደግሞ ለሐኪሙ 3 ሰቀል ብር ይከፍላል። ባርያ ከሆነ፣ 2 ሰቀል ብር ይከፍላል።]
  • 11፦ ማንም ነጻ የሆነውን ሰው እጅ ወይም እግር ቢሰብር፣ 20 ሰቀል ብር ከቤተሠቡ ፈልጎ ይከፍላል።
[1300፦ ማንም ነጻ የሆነውን ሰው እጅ ወይም እግር ቢሰብር፣ የተጎዳው ለዘለቄታ አቅመ ቢስ ከተደረገ፣ 20 ሰቀል ብር ይከፍለዋል። ለዘለቄታ አቅመ ቢስ ካልተደረገ፣ 10 ሰቀል ብር ይከፍለዋል።]
  • 12፦ ማንም ባርያ የሆነውን ሰው እጅ ወይም እግር ቢሰብር፣ 10 ሰቀል ብር ከቤተሠቡ ፈልጎ ይከፍላል።
[1300፦ ማንም ባርያ የሆነውን ሰው እጅ ወይም እግር ቢሰብር፣ የተጎዳው ለዘለቄታ አቅመ ቢስ ከተደረገ፣ 10 ሰቀል ብር ይከፍለዋል። ለዘለቄታ አቅመ ቢስ ካልተደረገ፣ 5 ሰቀል ብር ይከፍለዋል።]
  • 13፦ ማንም ነጻ የሆነውን ሰው አፍንጫ ቢያቋርጥ፣ 40 ሰቀል ብር ከቤተሠቡ ፈልጎ ይከፍላል።
[1300፦ ማንም ነጻ የሆነውን ሰው አፍንጫ ቢያቋረጥ፣ 30 ሚና* ብር ከቤተሠቡ ፈልጎ ይከፍላል።] [* = 1200 ሰቀል፤ «ሚና» የሚለው ግን ለ«ሰቀል» እንደተሳተ ይታስባል።]
  • 14፦ ማንም ባርያ የሆነውን ሰው አፍንጫ ቢያቋረጥ፣ 3 ሰቀል ብር ከቤተሠቡ ፈልጎ ይከፍላል።
[1300፦ ማንም ባርያ የሆነውን ሰው አፍንጫ ቢያቋረጥ፣ 15 ሚና* ብር ይከፍላል።] [* «ሚና» የሚለው ለ«ሰቀል» እንደተሳተ ይታስባል።]
  • 15፦ ማንም ነጻ የሆነውን ሰው ጆሮ ቢያቋረጥ፣ 12 ሰቀል ብር ከቤተሠቡ ፈልጎ ይከፍላል። [እንዲህም 1300 ግን «ከብቤተሠቡ ፈልጎ» አይልም።]
  • 16፦ ማንም ባርያ የሆነውን ሰው ጆሮ ቢያቋረጥ፣ 3 ሰቀል ብር ከቤትሠቡ ፈልጎ ይከፍላል።
[1300፦ ማንም ባርያ የሆነውን ሰው ጆሮ ቢያቋረጥ፣ 6 ሰቀል ብር ይከፍላል።]
  • 17፦ ማንም የነጻ ሴት ጽንስ እንዲጨናግፍ ቢያደርግ፣ 10ኛዋ ወር ከሆነ 10 ሰቀል ብር፤ 5ኛዋ ወር ከሆነ 5 ሰቀል ብር ከቤተሠቡ ፈልጎ ይከፍላል።
[1300፦ ማንም የነጻ ሴት ጽንስ እንዲጨናግፍ ቢያደርግ፣ 20 ሰቀል ብር ይከፍላል።]
  • 18፦ ማንም የሴት ባርያ ጽንስ እንዲጨናግፍ ቢያደርግ፣ 10ኛዋ ወር ከሆነ 5 ሰቀል ብር ይከፍላል።
[1300፦ ማንም የሴት ባርያ ጽንስ እንዲጨናግፍ ቢያደርግ፣ 10 ሰቀል ብር ይከፍላል።]
  • 19-ሀ፦ የሉዊያ ሰው ነጻ የሆነውን ሰው ወንድ ወይም ሴት ከሐቲ አገር ሰርቆ ወደ ሉዊያ / አርዛዋ አገር ቢመራው፣ በኋላም የተሠረቀው ሰው ባለቤት ቢያውቀው፣ ሌባው መላውን ቤቱን ያጣል።
  • 19-ለ፦ የሐቲ ሰው ሉዊያዊውን በሐቲ አገር እራሱ ውስጥ ሠርቆ ወደ ሉዊያ አገር ቢመራው፣ ቀድሞ 12 ሰዎች ይስጡ ነበር፣ አሁን ግን 6 ሰዎች ከቤተሠቡ ፈልጎ ይሰጣል።
  • 20፦ የሐቲ ሰው ኬጥያዊውን ባርያ ከሉዊያ አገር ሰርቆ ወዲህ ወደ ሐቲ አገር ቢመራው፣ በኋላም የተሰረቀው ሰው ጌታ ቢያውቀው፣ ሌባው 12 ሰቀል ብር ከቤትሰቡ ፈልጎ ይከፍለዋል።
  • 21፦ ማንም የሉዊያዊውን ሰው ወንድ ባርያ ከሉዊያ አገር ሰርቆ ወደ ሐቲ አገር ቢያምጣው፣ በኋላም ጌታው ቢያውቀው፣ ባርያውን ብቻ ይወስዳል፤ ካሣ አይኖርም።
  • 22-ሀ፦ ወንድ ባርያ ቢያመልጥ፣ ሰውም ቢያስመልሰው፣ በአቅራቢያውም ካገኘው፣ ባለቤቱ ላገኘው ጫማ ይሰጣል። ለ፦ ከወንዙ ወዲህ ከያዘው፣ 2 ሰቀል ብር ይከፍላል። ከወንዙ ማዶ ከያዘው፣ 3 ሰቀል ብር ይከፍለዋል።
  • 23-ሀ፦ ወንድ ባርያ ቢያመልጥ፣ ወደ ሉዊያም አገር ቢሄድ፣ ጌታው ለሚመልሰው ሰው 6 ሰቀል ብር ይከፍላል። ለ፦ ወንድ ባርያ ቢያመልጥ፣ ወደ ጠላትም አገር ቢሄድ፣ የሚመልሰው ሰው ለራሱ ይይዘዋል።
  • 24፦ ወንድ ወይም ሴት ባርያ ቢያመልጥ፣ ጌታው በምድጃው ያገኘውበት ሰውዬ የአንድ ወር ደመወዝ፣ ለወንድ 12 ሰቀል፣ ለሴት 6 ሰቀል ብር ይከፍላል።
[1300፦ ወንድ ወይም ሴት ባርያ ቢያመልጥ፣ ጌታው በምድጃው ያገኘውበት ሰውዬ የአንድ ዓመት ደመወዝ፣ ለወንድ 100 ሰቀል፣ ለሴት 50 ሰቀል ብር ይከፍላል።]
  • 25-ሀ፦ ማንም በሰው እቃ ወይም ጋን ውስጥ ቢረክስ፣ ቀድሞ 6 ሰቀል ብር ይከፍሉ ነበር፤ የረከሰው ለተበዳይ 3 ሰቀል ብር ይከፍልና 3 ሰቀል ብር ለንጉሡ ቤት ይወስዱ ነበር። ለ፦ አሁን ግን ንጉሡ ስለ ቤተ መንግሥቱ ድርሻ ይቅር ብለዋል። የረክሰው ሰው 3 ብር ለተበዳይ ከቤተሠቡ ፈልጎ ይከፍላል።
  • 26-ሀ፦ ሴት ወንድን ብትፈታ፣ ወንዱ [...ጽሕፈቱ ጠፍቷል...] ይሰጣታል፤ ሴቲቱም ስለዘርዋ ደመወዝ ትወስዳለች። ወንዱ ግን ርስቱንና ልጆቹን ይወስዳል [...]።
  • 26-ለ፦ ወንድ ግን ሴትን ቢፈታት፣ እስዋም ብት[...] [...] ይሸጣታል። የሚገዛትም ሰው 12 ሰቀል ብር ይከፍለዋል።
  • 27፦ ወንድ ሚስቱን ወስዶ ወደ ቤቱ ቢመራት፣ ጥሎሽዋን ወደ ቤቱ ይወስዳል። ሴቲቱ እዚያ ብትሞት፣ ንብረትዋን ሁሉ ያቃጥሉና ወንዱ ጥሎሽዋን ይወስዳል። በአባትዋ ቤት ብትሞትና ልጆች ቢኖሩ፣ ወንዱ ጥሎሽዋን አይወስድም።
  • 28-ሀ፦ ሴት ልጅ ለወንድ ከታጨች፣ ሌላ ወንድ ግን ከስዋ ጋር ከኮበለለ፣ ከስዋ ጋር የኮበለለው ሰው ለመጀመርያው ሰው ማጫውን ሁሉ ይመልስለታል። አባትና እናትዋ አይመልሱለትም። ለ፦ አባትና እናትዋ ለሌላ ወንድ ቢሰጡዋት፣ እነርሱ ይመልሱታል። ሐ፦ እንዲህ ለማድረግ ግን ካልወደዱ፣ አባትና እናትዋ ያስለያያቸዋል።
  • 29፦ ሴት ልጅ ለወንድ ከታጨች፣ እሱም ማጫ ቢክፍልላት፣ በኋላ ግን አባትና እናትዋ ስምምነቱን ቢከራክሩ፣ ከወንዱ ያስለዩዋታል፤ ማጫውን ግን ሁለት እጥፍ ይመልሳሉ።
  • 30፦ ወንድ ግን ሴት ልጂቱን በትዳር ሳይወስዳት እምቢ ቢላት፣ የከፈለውን ማጫ ያጣል።
  • 31፦ ነጻ ሰውና ሴት ባርያ ፍቅረኞች ሆነው አብረው ቢኖሩ፣ እንደ ሚስቱም ቢወስዳት፣ ቤተሠብና ልጆችንም ቢያድርጉ፣ በኋላ ግን ቢለያዩ ወይም ሁለቱ አዲስ ባለቤት ቢያገኙ ኖሮ፣ ቤቱን በእኩልነት ያካፍሉና ወንዱ ልጆቹን ወስዶ ሴቲቱ አንዱን ልጅ ትወስዳለች።
  • 32፦ ወንድ ባርያ ነጻ ሴትን ቢያግባት፣ ቤተሠብና ልጆችን ቢያድርጉ፣ ቤታቸውን ሲያካፍሉ ንብረታቸውን በእኩልነት ያካፍሉና ነጻ ሴቲቱ ብዙዎቹን ልጆች ወስዳ ወንድ ባርያው አንድ ልጅ ይወስዳል።
  • 33፦ ወንድ ባርያ ሴት ባርያን ቢያግባት፣ ልጆችም ቢኖራቸው፣ ቤታቸውን ሲያካፍሉ ንብረታቸውን በእኩልነት ያካፍላሉ። ሰት ባርያዋ ብዙዎቹን ልጆች ወስዳ ወንድ ባርያው አንድ ልጅ ይወስዳል።
  • 34፦ ወንድ ባርያ ለሴት ማጫ ከፍሎ እንደ ሚስቱ ቢወስዳት፣ ማንም ከባርነት ነጻ አያወጣቸውም።
  • 35፦ እረኛ ነጻ ሴትን ቢያግባት፣ ለሶስት አመት ባርያ ትሆናለች።
[1300፦ ካቦ ወይም እረኛ ማጫ ሳይከፍል ከነጻ ሴት ጋር ቢኮብለል፣ ለሶስት ዓመት ባርያ ትሆናለች።]
  • 36፦ ነጻ ወጣት ወደ ባርያ ማጫ ከፍሎ አማቹ ቢሆን፣ ማንም ከባርነት ነጻ አያወጣውም።
  • 37፦ ማንም ከሴት ጋር ቢኮብለል፣ የደጋፊዎችዋም ቡድን ቢያሳድዱት፣ 3 ወይም 2 ሰዎች ቢገደሉ፣ ካሣ የለም። «አንተ ተኲላ ሆነኻል።»
  • 38፦ ሰዎች በሙግት ቢያዙ፣ አንዱም ደጋፊ ወደነሱ ቢቅርብ፣ አንዱ ተሟጋች ቢናደድና ደጋፊው እንዲሞት ቢመታው፣ ካሣ የለም።
  • 39፦ ሰው የሌላውን ሰው ርስት ቢይዝም፣ የሚያስገደውም አገልግሎት ያደርጋል። አገግሎቱን እምቢ ቢል፣ መሬቱን ትቶ ያጣል፤ አይሸጠውም።
  • 40፦ የባለ-ዕጅ ግዴታ ያለበት ሰው ቢወድቅ፣ አገልግሎትም ያለበት ሰው ሥፍራውን ከወሰደ፣ አገልግሎት ያለበት ሰው «ይህ የኔ ባለ ዕጅ ግዴታ ነው፣ ሌላውም የኔ አገልግሎት ግዴታ ነው» ብሎ ይናገራል። ባለ-ዕጅ ግዴታ ስለ ነበረበት ሰው ርስት ማኅተም ያለበትን ውል ለራሱ ይቀበላል፤ ባለ-ዕጅ ግዴታውን ይይዛልና አገልግሎቱን ያደርጋል። ባለ-ዕጅ ግዴታውን ግን እምቢ ቢለው፣ ከባለ-ዕጅ ግዴታው የወድቀው ሰው ርስት ይሉትና የመንደሩ ሰዎች ይሠሩታል። ንጉሡ ስደተኛ ሰው ቢሰጥ፣ ርስቱን ይስጡትና እርሱ ባለ-ዕጅ ግዴታ ይሆናል።
  • 41፦ አገልግሎት ያለበት ሰው ቢወድቅ፣ ባለ-ዕጅ ግዴታም ያለበት ሰው በምትኩ ቢቆም፣ ባለ-ዕጅ ግደታ ያለበት ሰው «ይህ የኔ ባለ ዕጅ ግዴታ ነው፣ ሌላውም የኔ አገልግሎት ግዴታ ነው» ብሎ ይናገራል። አገልግሎት ስለ ነበረበት ሰው ርስት ማኅተም ያለበትን ውል ለራሱ ይቀበላል። ባለ-ዕጅ ግዴታውን ይይዛልና አገልግሎቱን ያደርጋል። አገልግሎቱን ለማድረግ ግን እምቢ ቢል፣ ከአገልግሎቱ የወደቀውን ሰው ርስት ለቤተ መንግስት ይወስዳሉ። አገልግሎቱም ይተዋል።
  • 42፦ ማንም ሰውን ቀጥሮት እሱም በጦርነት ዘመቻ ሄዶ ቢገደል፣ ደሞዙም ከተከፈለ፣ ካሣ የለም። ደሞዙ ካልተከፈለ ግን የቀጠረው አንድን ባርያ ይሰጣል።
[1300 እንዲህ ይጨምራል፦ «ለደመወዙም 12 ሰቀል ብር ይከፍላል። ለሴትም ደመወዝ 6 ሰቀል ብር ይከፍላል።»]
  • 43፦ ሰው ከበሬው ጋር ወንዙን እየተሻገረ፣ ሌላው ሰው ቢገፋው፣ የበሬውንም ጅራት ይዞ ወንዙን ቢሻገር፣ ወንዙ ግን የበሬውን ባለቤት ቢወስደው፣ የሞተው ሰው ወራሾች ያንን የገፋውን ሰው ይወስዱታል።
  • 44-ሀ፦ ማንም ሌላውን ሰው በእሳት እንዲወድቅ እንዲሞትም ካደረገ፣ በምላሽ ወንድ ልጁን ይሰጣል።
  • 44-ለ፦ ማንም በሰው ላይ የንጽሕና ሥነ ሥርዓት ቢያደርግ፣ ቅሬታውን በማቃጠል መጣያዎች ላይ ይጥለዋል። በሰው ቤት ውስጥ ቢጥለው ግን ጥንቆላ እና ለንጉሥ የሆነ ጉዳይ ነው።
  • 45፦ ማንም መሣርያዎችን ካገኘ፣ ወደ ባለቤታቸው መልሶ ያምጣቸዋል። እርሱም ወሮታ ይሰጠዋል። ያገኘው ግን ካልሰጣቸው፣ ሌባ ይባላል።
[1300፦ ማንም መሣርያዎችን ወይም በሬ፣ በግ፣ ፈረስ ወይም አህያ ካገኘ፣ ወደ ባለቤቱ መልሶ ይነዳውና ባለቤቱ ከዚያ ይመራዋል። ባለቤቱን ማግኘት ግን ካልቻለ፣ ምስክሮችን ያገኛል። በኋላ ባለቤቱ ሲያገኘው የጠፋውን በሙሉ ይወስዳል። ምስክሮችን ግን ባያገኝ፣ በኋላም ባለቤቱ ቢያገኘው፣ ሌባ ይባላልና ሶስት እጥፍ ካሣ ያደርጋል።]
  • 46፦ በመንደር ውስጥ ማንም እርሻ እንደ ርስቱ ድርሻ ቢይዝ፣ የእርሻዎች ትልቅ ክፍል ከተሰጠው፣ ቀረጥ ይሰጣል። የእርሻዎች ትንሹ ክፍል ግን ከተሰጠው፣ ቀረጥ አይሰጥም፣ ከአባቱ ቤት በኩል ይሰጡታል። ወራሽ ለራሱ ግል መሬት ቢቈርጥ፣ ወይም የመንደሩ ሰዎች ተጨማሪ መሬት ቢሰጡት፣ በግሉ መሬት ቀረጥ ይሰጣል።
[1300፦ በመንደር ውስጥ እንደ ርስት ድርሻ ማንም መሬትና አገልግሎት-ግዴታ ቢይዝ፣ መረቱ በመላው ከተሰጠው፣ ቀረጥ ይሰጣል። መሬቱ በመላው ካልተሰጠው፣ ትንሽ ድርሻ ብቻ ግን ከተሰጠው፣ ቀረጥ አይሰጥም። ከአባቱ ርስጥ በኩል ይሰጡታል። የወራሹ መሬት ከተተወ፣ የመንደሩም ሰዎች ሌላ የጋርዮሽን መሬት ከሰጡት፣ ቀረጥ ይሰጣል።]
  • 47-ሀ፦ ማንም መሬትን በንጉሣዊ ስጦታ ከያዘ፣ ቀረት ወይም አገልግሎት ሊሰጥበት የለበትም። ደግሞ ንጉሡ በንጉሣዊ ውጪ መብሉን ይሰጡታል።
[1300፦ ማንም መሬትን በንጉሣዊ ስጦታ ከያዘ፣ ቀረጡን ይሰጣል። ንጉሡ ግን ይቅርታ ከሰጡት፣ ቀረጡን አይሰጥም።]
  • 47-ለ፦ ማንም ባለ-ዕጅ ግዴታ ያለበትን ሰው ርስት ሁሉ ከገዛ፣ ቀረጥ ይሰጣል። የርስቱን ትልቅ ክፍል ብቻ ከገዛ ግን፣ ቀረጥ ሊሰጥበት የለበትም። ለራሱ ግን ግል መሬት ቢቈርጥ፣ ወይም የመንደሩ ሰዎች መሬት ቢሰጡት፣ ቀረጡን ይሰጣል።
[1300፦ ማንም የባለ-ዕጅ ግዴታ ሰው መሬት ሁሉ ከገዛ፣ የመሬቱም ቀድሞ ባለቤት ቢሞት፣ አዲሱ ባለቤት ንጉሡ የወሰኑትን አገልግሎት ሁሉ ያደርጋል። የቀድሞ ባለቤት ግን ገና ቢኖር፣ ወይም ለቀድሞው ባለቤት በዚያም ሆነ በሌላ አገር ርስት ቢኖረው፣ አገልግሎት አያደርግም።]
[1300፦ ማንም የባለ-ዕጅ ግዴታ ሰው መሬት ሁሉ ከገዛ፣ የመሬቱም ቀድሞ ባለቤት ቢሞት፣ አዲሱ ባለቤት ንጉሡ የወሰኑትን ቀረጥ ሁሉ ይሰጣል። በተጨማሪ የሌላውን ሰው ርስት ከገዛ፣ ቀረጥ አይሰጥበትም። መሬቱ ከተተወ ወይም የመንደሩ ሰዎች ሌላ መሬት ቢሰጡት፣ ቀረጡን ይሰጣል።]
  • 48፦ ተወጋዥ ሰው [?] ቀረጥ ይሰጣል። ማንም ከተወጋዥ ሰው ጋር አይገበያይ። ማንም ልጁን፣ መሬቱን፣ የወይን ሐረጉን አይግዛ። ማንም ከተወጋዥ ሰው ጋር የሚገበያይ፣ የመግዣ ዋጋውን ያጣል፣ ተወጋዡም ሰው የሸጠውን በምላሽ ይወስዳል።
  • 49፦ ተወጋዥ ሰው ቢሰርቅ፣ ካሣ አይኖርም። [...] ቢሆን ግን፣ የርሱ [...] ብቻ ካሣ ይሰጣል። ስርቆት መስጠት ከነበረባቸው፣ ሁላቸው ጠማማ ወይም ሌቦች ይሁኑ ነበር። ይኸኛው ያንን ይይዝ፣ ያም ይኸኛውን ይይዝ ነበር። የንጉሡን ሥልጣን ይገልብጡ ነበር።
  • 50፦ በኔሪክ፣ አሪና ወይም ዚፕላንታ ውስጥ [...] የሚያድርግ ሰው ፣ በማናቸውም መንደር ቄስ የሆነውም [...] ቤታቸው (ከቀረጥ) ይቅርታ አላቸው፣ ጓደኞቻቸውም ቀረጥ ይሰጣሉ። በአሪና 11ኛው ወር ሲደርስ፣ በበሩ ላይ ማምለኪያ ዋልታ ያቆመው እንዲሁም ይቅርታ አለው።
  • 51፦ ቀድሞ በአሪና ውስጥ ሸማኔ የሆነ ሰው ቤት ይቅርታ ነበረው፣ እንዲሁም ጓደኞቹና ዘመዶቹ ይቅርታ ነበራቸው። አሁን የሱ ቤት ብቻ ይቅርታ አለው፤ ጓደኞቹና ዘመዶቹ ግን ቀረጥ ይሰጣሉ። በዚፓላንቲያ ደግሞ ልክ እንደዚህ ይሆናል።
  • 52፦ የድንጋይ መፍለጫ ባርያ፣ የመስፍን ወይም የመቃ ቅርጽ አርማ ለመልበስ መብት ያለው ሰው ባርያ፤ እንደነዚህ ካሉት ሰዎች ማንም የባለ-ዕጅ ግዴታ ካለባቸው ሰዎች መካከል መሬት ቢኖረው፣ እሱም ቀረጡን ይሰጣል።
  • 53፦ ባለ-ዕጅ ግዴታ ያለበት ሰውና ጓደኛው አብረው ቢኖሩ፣ በጸብ ቢለያዩም፣ ቤተሠባቸውን ያካፍላሉ። በርስታቸው ላይ አሥር ሰዎች ካሉ፣ ባለ-እጅ ግዴታ ያለበት ሰው 7ቱን ተቀብሎ ጓደኛው ሦስቱን ይቀበላል። በርስታቸው ላይ ያሉት በሬና በግ እንዲሁም በዚያው መጠን ያካፍላሉ። ማንም ንጉሣዊ ስጦታ በጽላት ከያዘ፣ የቆየውን መሬት ቢያካፍሉ፣ ባለ-ዕጅ ግዴታ ያለበት ሰው 2 ክፍሎችና ጓደኛው አንዱን ክፍል ይወስዳል።
  • 54፦ ቀድሞ፣ [...] ጭፍሮች፣ የሳላ፣ ታማልኪ፣ ሃትራ፣ ዛልፓ፣ ታሺኒያ እና ሄሙዋ ጭፍሮች፣ ቀስተኞች፣ አናጢዎች፣ የሠረገላ ጦረኞችና የነሱ [...] ሰዎች ቀረጡን አይሰጡም ነበር፣ ወይም አገልግሎቱን አያደርጉም ነበር።
  • 55፦ አገልግሎቱ ያለባቸው አንዳንድ ኬጥያውያን ሲቀርቡ፣ ለንጉሡ አባት ክብር ሰጡና እንዲህ አሉ፦ «ማንም ደመወዝ አይከፍለንም። 'እንደ አገልግሎት ሥራችሁን ለመፈጽም ያለባችሁ ሰዎች ናችሁ' ይሉናል።» የንጉሡም አባት ወደ ማህበሩ ገብተው ከማኅተማቸው ሥር እንዲህ ተናገሩ፦ «እናንተ ልክ እንደ ባልደረባዎቻችሁ አገልግሎቱን መፈጽማችሁን ሳታቋርጡ ይኖርባችኋል!»
  • 56፦ ከመዳብ አንጥረኞቹ፣ ማንም በረዶ ከማምጣት፣ አምባና ንጉሣዊ መንገድ ከመሥራት፣ ወይም ወይን ሐረጉን ከማምረት ይቅርታ የለውም። የአጸድ ጠባቂዎቹም እንዲሁ በነዚህ ሥራዎች ቀረት ይሰጣሉ።
  • 57፦ ማንም ወይፈንን ቢሰርቅ፣ አዲስ ጥጃ ከሆነ፣ «ወይፈን» አይደለም፤ አጎሬሳ ጥጃ ከሆነ፣ «ወይፈን» አይደለም፤ የኹለት ዓመት በሬ ከሆነ፣ ያው «ወይፈን» ነው። ቀድሞ 30 በሬዎች ይስጡ ነበር። አሁን ግን ከቤተሠቡ ፈልጎ 15 በሬዎች ይሰጣል፤ እነሱም 5 የኹለት ዓመት፣ 5 አጎሬሳና 5 አዲስ ጥጃዎች ይሆናሉ።
  • 58፦ ማንም ድንጉላ ፈረስን ቢሰርቅ፣ አዲስ ግልገል ከሆነ፣ «ድንጉላ» አይደለም፤ አጎሬሳ ከሆነ፣ «ድንጉላ» አይደለም፤ የኹለት ዓመት ከሆነ፣ ያው «ድንጉላ» ነው። ቀድሞ 30 ፈረሶች ይስጡ ነበር። አሁን ግን ከቤተሠቡ ፈልጎ 15 ፈረሶች ይሰጣል፤ እነሱም 5 የኹለት ዓመት፣ 5 አጎሬሳና 5 አዲስ ግልገሎች ይሆናሉ።
  • 59፦ ማንም አውራ በግ ቢሰርቅ፣ ቀድሞ 30 በጎች ይስጡ ነበር። አሁን ግን ከቤተሠቡ ፈልጎ 15 በጎች ይሰጣል፤ እነሱም 5 አንስቶች፣ 5 ኩልሾችና 5 ጠቦት ይሆናሉ።
  • 60፦ ማንም ወይፈን አግኝቶ ቢያኮላሸው፣ ባለቤቱ ሲያገኘው፣ ከቤተሠቡ ፈልጎ 7 በሬዎች ይሰጣል፤ እነሱም 2 የኹለት ዓመት፣ 3 አጎሬሳና 2 አዲስ ጥጃዎች ይሆናሉ።
  • 61፦ ማንም ድንጉላ አግኝቶ ቢያኮላሸው፣ ባለቤቱ ሲያገኘው፣ ከቤተሠቡ ፈልጎ 7 ፈረሶችች ይሰጣል፤ እነሱም 2 የኹለት ዓመት፣ 3 አጎሬሳና 2 አዲስ ግልገሎች ይሆናሉ።
  • 62፦ ማንም አውራ በግ አግኝቶ ቢያኮላሸው፣ ባለቤቱ ሲያገኘው፣ ከቤተሠቡ ፈልጎ 7 በጎች ይሰጣል፤ እነሱም 2 አንስቶች፣ 3 ኩልሾችና 2 ጠቦት ይሆናሉ።
  • 63፦ ማንም የማረሻ በሬ ቢሰርቅ፣ ቀድሞ 15 በሬዎች ይስጡ ነበር። አሁን ግን ከቤተሠቡ ፈልጎ 10 በሬዎች ይሰጣል፤ እነሱም 3 የኹለት ዓመት፣ 3 አጎሬሳና 4 አዲስ ጥጃዎች ይሆናሉ።
  • 64፦ ማንም የአጋሠሥ ፈረስ ቢሰርቅ፣ ልክ እንዲህ (እንደ ማረሻ በሬ) ነው።
  • 65፦ ማንም የተሠለጠነ ወጠጤ ፍየል፣ የተሰለጠነ አጋዘን፣ ወይም የተሠለጠነ የተራራ ፍየል ቢሰርቅ፣ ልክ እንደ ማረሻ በሬ ስርቆት ነው።
  • 66፦ የማረሻ በሬ፣ የአገሣሥ ፈረስ፣ ላም ወይም ባዝራ ወደ ሌላ በረት ቢኮብለል፣ ወይም የተሠለጠነ ወጣጤ፣ አንስት በግ ወይም ኩልሽ በግ ወደ ሌላ ጋጣ ቢኮብለል፣ ባለቤቱም ቢያገኘው፣ በምላሽ በሙሉ ይወስደዋል። የጋጣው ባለቤት እንደ ሌባ እንዲታሠር አያደርግም።
  • 67፦ ማንም ላምን ቢሰርቅ፣ ቀድሞ 12 በሬዎች ይስጡ ነበር። አሁን ግን ከቤተሠቡ ፈልጎ 6 በሬዎች ይሰጣል፤ እነሱም 2 የኹለት ዓመት፣ 2 አጎሬሳና 2 አዲስ ጥጃዎች ይሆናሉ።
  • 68፦ ማንም ባዝማ ቢሰርቅ፣ እንዲህ ተመሳሳይ (እንደ ላም) ነው።
  • 69፦ ማንም አንስት ወይም ኩልሽ በግ ቢሰርቅ፣ ቀድሞ 12 በጎች ይስጡ ነበር። አሁን ግን ከቤተሠቡ ፈልጎ 6 በጎች ይሰጣል፤ እነሱም 2 አንስቶች፣ 2 ኩልሾችና 2 ጠቦት ይሆናሉ።
  • 70፦ ማንም በሬ፣ ፈረስ፣ በቅሎ ወይም አህያ ቢሰርቅ፣ ባለቤቱ ሲያገኘው በሙሉ ይወስደዋል። በተጨማሪ ሌባው ሁለት እጥፍ ከቤትሠቡ ፈልጎ ይሰጠዋል።
  • 71፦ ማንም በሬ፣ ፈረስ ወይም በቅሎ ቢያገኝ፣ ወደ ንጉሡ በር ይነዳዋል። በአገር ቤት ቢያገኘው፣ ወደ ሽማግሌዎቹ ይነዱታል። ያገኘው ልጓም ይጭነዋል። ባለቤቱ ሲያገኘው በሙሉ ይወስደዋል፤ ያገኘውን ግን እንደ ሌባ እንዲታሠር አያደርግም። ያገኘው ግን ወደ ሽማግሌዎቹ ባያቀርበው፣ ሌባ ይባላል።
  • 72፦ በሬ በሰው ርስት ላይ ሞቶ ቢገኝ፣ ባለርስቱ 2 በሬ ከቤተሠቡ ፈልጎ ይሰጣል።
  • 73፦ ማንም በሬን በሕይወቱ ሳለ ቢ[...]፣ ልክ እንደ ስርቆት ነው።
  • 74፦ ማንም የበሬን ቀንድ ወይም እግር ቢሰብር፣ ያንን በሬ ለራሱ ወስዶ ደህና በሬን ለተጎዳው በሬ ባለበት ይሰጣል። የበሬው ባለቤት «በሬዬን እወስዳለሁ» ካለ፣ በሬውን ይወስድና በዳዩ 2 ሰቀል ብር ይከፍላል።
  • 75፦ ማንም በሬ፣ ፈረስ፣ በቅሎ ወይም አህያን ቢያሥር፣ (እንስሳውም) ቢሞት፣ ወይም ተኩላ ቢበላው፣ ወይም ቢጠፋ፣ በሙሉ ይሰጠዋል። እሱ ግን፦ «በአምላክ እጅ ሞተ» ካለ፣ እንደዛ ብሎ ይምላል።
  • 76፦ ማንም በሬ፣ ፈረስ፣ በቅሎ ወይም አህያን ቢከራይ፣ (እንስሳውም) በቦታው ቢሞት፣ ያምጣዋልና ደግሞ ኪራዩን ይከፍላል።
  • 77-ሀ፦ ማንም እርጉዝ ላም እንድትጨናገፍ ቢመታት፣ 2 ሰቀል ብር ይከፍላል። ማንም እርጉዝ ፈረስ እንድትጨናገፍ ቢመታት፣ 3 ሰቀል ብር ይከፍላል። ለ፦ ማንም የበሬ ወይም የአህያን ዓይን ቢያሳውር፣ 6 ሰቀል ብር ከቤተሠቡ ፈልጎ ይከፍላል።
  • 78፦ ማንም በሬ ቢከራይ፣ በሱም ላይ የቆዳ [...] ወይም የቆዳ [...] ቢያደርግ፣ ባለቤቱም ቢያገኘው፣ አንድ ፓሪሹ (ሀምሳ ሊተር) ገብስ ይከፍላል።
  • 79፦ በሬዎች ወደ ሌላ ሰው እርሻ ቢገቡ፣ ባለ እርሻውም ቢያገኛቸው፣ ለአንዱ ቀን፣ ከዋክብት እስከሚወጡ ድረስ፣ እነሱን ማሠር ይችላል። ከዚያም ወደ ባለቤታቸው ይነዳቸዋል።
  • 80፦ ማንም እረኛ በግ ወደ ተኩላ ቢጥለው፣ ባለቤቱ ሥጋውን ይወስዳል፤ እረኛው ግን ለምዱን ይወስዳል።
  • 81፦ ማንም የሰባ ዐሳማ ቢሰርቅ፣ ቀድሞ አርባ ሰቀል ብር ይከፍሉ ነበር። አሁን ግን 12 ሰቀል ብር ከቤተሠቡ ፈልጎ ይከፍላል።
  • 82፦ ማንም የአጥር ግቢ ዐሳማ ቢሰርቅ፣ ከቤተሠቡ ፈልጎ 6 ሰቀል ብር ይከፍላል።
  • 83፦ ማንም እርጉዝ ዐሳማ ቢሰርቅ፣ ስድስት ሰቀል ብር ይከፍልና ግልገሎቹን ይቆጥራሉ፤ ለየሁለቱም ግልገሎች አንድ ፓሪሹ (50 ሊተር) ገብስ ከቤተሠቡ ፈልጎ ይሰጣል።
  • 84፦ ማንም እርጉዝ ዐሳማ መትቶ ቢገድላት፣ ልክ እንዲህ (እንደ ስርቆት) ይሆናል።
  • 85፦ ማንም የዐሳማ ግልገል ለይቶ ቢሰርቅ፣ 2 ፓሪሹ (መቶ ሊተር) ገብስ ይሰጣል።
  • 86፦ ዐሳማ ወደ እህል ክምችት፣ እርሻ ወይም አጸድ ቢገባ፣ የእህል ክምችቱም፣ የእርሻም ሆነ አጸድ ባለቤት መትቶ ቢገድለው፣ ወደ (እንስሳው) ባለቤት ይመልሰዋል። ካልመለሰው ሌባ ይባላል።
  • 87፦ ማንም የእረኛውን ውሻ መትቶ ቢገድለው፣ ሃያ ሰቀል ብር ከቤተሠቡ ፈልጎ ይከፍላል።
  • 88፦ ማንም የአዳኙን ውሻ መትቶ ቢገድለው፣ 12 ሰቀል ብር ከቤተሠቡ ፈልጎ ይከፍላል።
  • 89፦ ማንም የአጥር ግቢ ውሻ መትቶ ቢገድለው፣ አንድ ሰቀል ብር ከቤተሠቡ ፈልጎ ይከፍላል።
  • 90፦ ውሻ ጮማ ቢበላ፣ የጮማውም ባለቤት ውሻውን ቢያገኝ፣ ይገድለውና ጮማውን ከሆዱ ያውጣው። ስለ ውሻው ምንም ካሳ አይሆንም።
  • 91፦ ማንም ንቦችን በመንጋ ቢሰርቃቸው፣ ቀድሞ [...] ሰቀል ብር ይከፍሉ ነበር፤ አሁን ግን አምስት ሰቀል ብር ከቤተሠቡ ፈልጎ ይከፍላል።
  • 92፦ ማንም 2 ወይም 3 የንብ ቀፎ ቢሰርቅ፣ ቀድሞ ሌባው ለንቦች መንደፍ ይጋለጥ ነበር። አሁን ግን 6 ሰቀል ብር ይከፍላል። ማንም የንብ ቀፎ ቢሰርቅ፣ እቀፎ ውስጥ ግን ንብ ከሌለበት፣ 3 ሰቀል ብር ይከፍላል።
  • 93፦ ነጸ ሰው ወደ ቤቱ ሳይገባ በመጀመርያው ቢይዙት፣ 12 ሰቀል ብር ይከፍላል። ባርያ ወደ ቤቱ ሳይገባ በመጀመርያው ቢይዙት፣ 6 ሰቀል ብር ይከፍላል።
  • 94፦ ነጻ ሰው ቤትን ነድሎ ቢሰርቅ፣ በሙሉ ይከፍላል። ቀድሞ ለስርቆቱም ቅጣት አርባ ሰቀል ብር ይከፍሉ ነበር፤ አሁን ግን 12 ሰቀል ብር ይከፍላል። ብዙ ቢሰርቅ፣ ብዙ ያስገዱታል። ጥቂት ቢሰርቅ፣ ጥቂት ያስገዱታል። ከቤተሠቡ ፈልጎ ይከፍላል።
  • 95፦ ባርያ ቤትን ነድሎ ቢሰርቅ፣ በሙሉ ይከፍላል። ስለ ስርቆቱም 6 ሰቀል ብር ይከፍላል። የባርያውን አፍንጫና ጆሮች ያጥፉና ወደ ጌታው ይመልሱታል። ብዙ ቢሰርቅ፣ ብዙ ያስገዱታል፤ ጥቂት ቢሰርቅ፣ ጥቂት ያስገዱታል። ጌታው «እኔ ካሣውን እከፍላለሁ» ካለ፣ ይክፈለው። እምቢ ካለ ግን፣ ያንን ባርያ ያጣል።
  • 96፦ ነጻ ሰው በጎተራ ጉድጓድ ነድሎ ቢገባ፣ በጎተራውም ጉድጓድ እኅልን ካገኘ፣ የጎተራውን ጉድጓድ በእህል ይሞላና 12 ሰቀል ብር ከቤተሠቡ ፈልጎ ይከፍላል።
  • 97፦ ባርያ በጎተራ ጉድጓድ ነድሎ ቢገባ፣ በጎተራውም ጉድጓድ እኅልን ካገኘ፣ የጎተራውን ጉድጓድ በእህል ይሞላና 6 ሰቀል ብር ከቤተሠቡ ፈልጎ ይከፍላል።
  • 98፦ ነጻ ሰው ቤትን ቢያቃጥል፣ ያንን ቤት ታድሶ ያገንበዋል። በቤቱም ውስጥ የጠፋው ሁሉ፣ ሰው፣ በሬ ወይም በግ ቢሆን፣ ጉዳት ነው። ካሳውን ይከፍላል።
  • 99፦ ባርያ ቤትን ቢያቃጥል፣ ጌታው ካሣውን ይከፍልለታል፤ የባርያውንም አፍንጫና ጆሮች ያጥፉና ወደ ጌታው ይመልሱታል። ጌታው ግን ካሣውን ባይከፍል፣ ያንን ባርያ ያጣል።
  • 100፦ ማንም ዳስን ቢያቃጥል፣ የባለቤቱን ከብት ያመግብና እስከሚከተለው ፀደይ ድረስ ያምጣቸዋል። ዳሱን ይመልሳል። ገለባ ካልነበረበት፣ ዳሱን ታድሶ ያገንበዋል።

ክፍል ፪ 101-200 «ማንም ሐረግ...»

ለማስተካከል
  • 101፦ ማንም ሐረግ፣ የወይን ሐረግ ቅርንጫፍ፣ [...] ወይም ነጭ ሽንኩርት ቢሰርቅ፣ ቀድሞ 1 ሰቀል ብር ለአንድ ሐረግ፣ 1 ሰቀል ብር ለአንድ ወይን ሐረግ ቅርንጫፍ፣ 1 ሰቀል ብር ለአንድ ካርፒና (?)፣ 1 ሰቀል ብር ለአንድ ነጭ ሽንኩርት ክፍል ይከፍሉ ነበር። እነርሱም ጦር በርሱ [...] ላይ ይጥላሉ፤ ቀድሞ እንዲህ ይሄዱ ነበር። አሁን ግን ነጻ ሰው ከሆነ፣ 6 ሰቀል ብር ይከፍላል። ባርያ ከሆነ ግን፣ 3 ሰቀል ብር ይከፍላል።
  • 102፦ ማንም እንጨት ከ[...] ኩሬ ቢሰርቅ፣ 1 መክሊል (31 ኪሎግራም) እንጨት ቢሠርቅ 3 ሰቀል ብር ይከፍላል፤ 2 መክሊል እንጨት ቢሠርቅ 6 ሰቀል ብር ይከፍላል፤ 3 መክሊል እንጨት ቢሰርቅ የንጉሡ ችሎት ጉዳይ ይሆናል።
  • 103፦ ማንም አትክልት ቢሰርቅ፣ የ0.25 ካሬ ሜትር ተከላ ቢሆን ታድሶ ይተክለዋልና 1 ሰቀል ብር ይከፍላል። የ0.5 ካሬ ሜትር ተከላ ቢሆን ታድሶ ይተክለዋልና 2 ሰቀል ብር ይከፍላል።
  • 104፦ ማንም የእንኮይ ወይም የሸክኒት ገረብ ዛፍ ቢቈርጠው፣ [...] ሰቀል ብር ከቤተሠቡ ፈልጎ ይከፍላል።
  • 105፦ ማንም እርሻን ቢያቃጥል፣ እሳቱም በሐረጉ ወይን ያለበትን ቦታ ቢይዝ፣ ሐረግ፣ የቱፋሕ፣ እንኮይ ወይም የሸክኒት ገረብ ዛፍ ቢቃጠል፣ ስድስት ሰቀል ብር ለየዛፉ ይከፍላል። ታድሶ ይተክለዋል። ከቤተሠቡም ይፈልገዋል። ባርያ ቢሆን፣ ሦስት ሰቀል ብር ይከፍላል።
  • 106፦ ማንም ፍም ወደ እርሻው ቢሸከም፣ ሲያፍራም ቢያቃጥለው፣ እሳቱን የጀመረው እራሱ የተቃጠለውን እርሻ ይወስዳል። ለተቃጠለውም እርሻ ባለቤት ደህና እርሻ ይሰጠዋል፣ ያጭደውማል።
  • 107፦ ማንም በጎቹን በሚያፍራ ወይን ሐረግ ቦታ ውስጥ ቢያስገባው፣ ቢያበላሹትም፣ ወይኑ በሓረግ ካለ፣ ለአንድ ኢኩ (3600 ካሬ ሜትር) 10 ሰቀል ብር ከቤተሠቡ ፈልጎ ይከፍላል። ባዶ ቢሆን ግን፣ 3 ሰቀል ብር ይከፍላል።
  • 108፦ ማንም የወይን ሐረግ ቅርንጫፎች በአጥር ከታጠረ ወይን ሐረግ ቦታ ቢሠርቅ፣ መቶ ሐረጎች ቢሰርቅ ስድስት ሰቀል ብር ከቤተሠቡ ፈልጎ ይከፍላል። የወይን ሓረግ ቦታው ግን ካልታጠረ፣ የወይን ሐረግ ቅርንጫፎችንም ቢሠርቅ፣ ሦስት ሰቀል ብር ይከፍላል።
  • 109፦ ማንም የፍራፍሬ ገረብ ዛፎችን ከመስኖአቸው ቢያቋርጥ፣ መቶ ዛፎች ካሉ 6 ሰቀል ብር ይከፍላል።
  • 110፦ ማንም ሸክላ ከጉድጓድ ቢሰርቅ፣ እንደ ሰረቀው መጠን እንዲህ ተጨማሪ ይሰጣል።
  • 111፦ ማንም ሸክላ እንደ ምስል ቢሠራው፣ ጥንቆላ ነውና የንጉሡ ችሎት ጉዳይ ነው።
  • 112፦ የጠፋውን ባለ-እጅ ግዴታ ያለበትን ሰው መሬት ለስደተኛ ቢሰጡ፣ ለሦስት ዓመት አገልግሎቱን አያደርጉም፤ በአራተኛው ዓመት ግን አገልግሎቱን ማድረግ ይጀምራል፤ ባለ-እጅ ግዴታ ያለባቸውንም ሰዎች ይባበራል።
  • 113፦ ማንም ሐረግ ቢቈርጥ፣ የተቈረጠውን ሐረግ ለራሱ ይወስድና ለሐረጉ ባለቤት የደህና ሐረግ ጥቅም ይሰጣል። የተቈረጠው ሐረግ መጀመርያ ባለቤት ሐረጉ እስኪድን ድረስ ፍሬውን ከአዲሱ ሐረግ ያመርታል።
  • 114-118፦ [...ጽሕፈቱ ጠፍቷል...]
  • 119፦ ማንም የተሠለጠነውን የኩሬ ወፍ (ዳክዬን)፣ ወይም የተሠለጠነውን የተራራ ፍየልን ቢሠርቅ፣ ቀድሞ አርባ ሰቀል ብር ይከፍሉ ነበር፤ አሁን ግን 12 ሰቀል ብር ከቤተሠቡ ፈልጎ ይከፍላል።
  • 120፦ ማንም የተ[...] አዕዋፍ ቢሰርቅ፣ 10 አዕዋፍ ካሉ፣ አንድ ሰቀል ብር ይከፍላል።
  • 121፦ አንድ ነጻ ሰው ማረሻን ቢሠርቅ፣ ባለቤቱም ቢያገኘው፣ «አንገቱን በ[....]ው ላይ ተደርጎ በበሬዎቹ ይገደላል»፦ ቀድሞ እንዲህ ይካሄዱ ነበር። አሁን ግን፣ 6 ሰቀል ብር ከቤትሠቡ ፈልጎ ይከፍላል። ባርያ ቢሆን 3 ብር ይከፍላል።
  • 122፦ ማንም ጋሪ ከነተቀጥላዎቹ ሁሉ ቢሰርቅ፣ ቀድሞ 1 ሰቀል ብር ይከፍሉ ነበር፣ አሁን ግን [...] ሰቀል ብር ከቤቱ ፈልጎ ይከፍላል።
  • 123፦ ማንም [...] ቢሰርቅ፣ [...] [...] አሁን ግን ሦስት ሰቀል ብር ከቤተሠቡ ፈልጎ ይከፍላል።
  • 124፦ ማንም የ[...] ዛፍ ቢሰርቅ፣ ሦስት ሰቀል ብር ከቤተሠቡ ፈልጎ ይከፍላል። ማንም ጋሪውን በሸክም ቢጭን፣ በሜዳው ላይ ቢተወው፣ አንድ ሰውም ቢሰርቀው፣ ሦስት ሰቀል ብር ከቤተሠቡ ፈልጎ ይከፍላል።
  • 125፦ ማንም የእንጨት ውሃ ገንዳ ቢሰርቅ፣ [...] እና አንድ ሰቀል ብር ይከፍላል። ማንም የቆዳ [...] ወይም የቆዳ [...] ቢሰርቅ፣ አንድ ሰቀል ብር ይከፍላል።
  • 126፦ ማንም የእንጨት [...] በቤተመንግሥት በር ቢሰርቅ፣ ስድስት ሰቀል ብር ይከፍላል። ማንም የነሐስ ጦር በቤተመንግሥት በር ቢሰርቅ፣ ይገደላል። ማንም የመዳብ ቅትርት ቢሰርቅ፣ 25 ሊተር ገብስ ይሰጣል። ማንም ከአንድ የጨርቅ ጥቅል ፈትሎችን ቢሰርቅ፣ አንድ የሱፍ ጨርቅ ጥቅል ይሰጣል።
  • 127፦ ማንም በጸብ መዝጊያ በርን ቢሰርቅ፣ ከቤት የሚጠፋውን ሁሉ ታድሶ ይመልሳል፤ አርባ ሰቀል ብርም ከቤተሰቡ ፈልጎ ይከፍላል።
  • 128፦ ማንም ጡብን ቢሰርቅ፣ እንደ ሰረቀው ቁጥር ሁለት እጥፍ ይሰጣል። ማንም ድንጊያ ከቤት መሠረት ቢሰርቅ፣ ለ2 ድንጊያ 10 ድንጊያ ይሰጣል። ማንም ጽላት ወይም የ[...] ድንጋይ ቢሰርቅ፣ ሁለት ሰቀል ብር ይከፍላል።
  • 129፦ ማንም የፈረስ ወይም የበቅሎ የቆዳ [...]፣ የቆዳ [....]፣ ወይም የነሓስ ደወል ቢሰርቅ፣ ቀድሞ አርባ ሰቀል ብር ይከፍሉ ነበር፤ አሁን ግን 12 ሰቀል ብር ከቤተሠቡ ፈልጎ ይከፍላል።
  • 130፦ ማንም የበሬ ወይም የፈረስ [...]ኦች ቢሰርቅ፣ [...] ሰቀል ብር ከቤተሠቡ ፈልጎ ይከፍላል።
  • 131፦ ማንም የቆዳ ልጓም ቢሰርቅ፣ ስድስት ሰቀል ብር ከቤተሠቡ ፈልጎ ይከፍላል።
  • 132፦ ነጻ ሰው [...] ቢሰርቅ፣ ስድስት ሰቀል ብር ከቤተሠቡ ፈልጎ ይከፍላል። ባርያ ቢሆን ሦስት ሰቀል ብር ይከፍላል።
  • 133፦ ነጻ ሰው [...] ቢሰርቅ፣ [...] ሰቀል ብር ከቤተሠቡ ፈልጎ ይከፍላል። ባርያ ቢሆን [...] ሰቀል ብር ይከፍላል።
  • 142፦ ማንም [...] ቢነዳ፣ ማንም ሽክርክሩን ቢሰርቅ፣ ለየሽክርክሩ 25 ሊተር ገብስ ይሰጣል። ባርያ ቢሆን፣ ለየሽክርክሩ [...] ሊተር ገብስ ይሰጣል።
  • 143፦ ነጻ ሰው የመዳብ መቀስ ወይም የመዳብ ሞረድ ቢሰርቅ፣ ስድስት ሰቀል ብር ከቤተሠቡ ፈልጎ ይከፍላል። ባርያ ቢሆን ሦስት ሰቀል ብር ይከፍላል።
  • 144፦ የጸጉር አስተካካይ የመዳብ [...] ለባልደረባው ቢሰጥ፣ እሱም ቢያበላሸው፣ በሙሉ ታድሶ ይመልሰዋል። ማንም ረቂቅ ጨርቅ በ[...] ቢቈርጥ፣ 10 ሰቀል ብር ይከፍላል። ማንም [...] ቢቈርጥ፣ 5 ሰቀል ብር ይከፍላል።
  • 145፦ ማንም የበሬ ጎተራ ቢገንባ፣ ቀጣሪው 6 ሰቀል ብር ይከፍለዋል። እሱ [...] ቢያስቀር፣ ደመወዙን ያጣል።
  • 146-ሀ፦ ማንም ቤት፣ መንደር፣ አጸድ ወይም መስክ እንዲሸጥ ቢያቀርብ፣ ሌላውም ሂዶ ሽያጩን ቢያሰናከል፣ በፈንታውም የራሱን ሽያጭ ቢያድርግ፣ ለበደሉ ቅጣት 40 ሰቀል ብር ይከፍላል፣ [...]ውንም በመጀመርያው ዋጋ ይገዛል። ለ፦ ማንም የ[...] ሰው ለሽያጭ ቢያቀርብ፣ ሌላ ሰውም ሂዶ ሽያጩን ቢያሰናከል፣ ስለበደሉ 10 ሰቀል ብር ይከፍላል። ሰውዬውን በመጀመርያው ዋጋ ይገዛል።
  • 147፦ ማንም ባለሙያ ያልሆነውን ሰው ለሽያጭ ቢያቀርብ፣ ሌላ ሰውም ሂዶ ሽያጩን ቢያሰናከል፣ ለበደሉ ቅጣት 5 ሰቀል ብር ይከፍላል።
  • 148፦ ማንም በሬ፣ ፈረስ፣ በቅሎ ወይም አህያ ለሽያች ቢያቀርብ፣ ሌላ ሰውም ሽያጩን ቢያስቀድመው፣ ለበደሉ ቅጣት [...] ሰቀል ብር ይከፍላል።
  • 149፦ ማንም የተሠለጠነውን ሰው ሸጥቶ «ሞቷል» ቢል፣ ገዢው ግን ፈልጎ ቢያገኘው፣ ለራሱ ይወስደዋል፤ በተጨማሪም ሻጩ ሁለት ሰዎችን ከቤተሠቡ ፈልጎ ይሰጠዋል።
  • 150፦ ወንድ እራሱን ለደመወዝ ቢያከራይ፣ ቀጣሪው [...] ሰቀል ብር ለአንድ ወር ይከፍላል። ሴት እራስዋን ለደመወዝ ብታከራይ፣ ቀጣሪዋ [...] ሰቀል ለአንድ ወር ይከፍላል።
  • 151፦ ማንም የማረሻን በሬ ቢከራይ፣ አንድ ሰቀል ብር ለአንድ ወር ይከፍላል። ማንም [...] ቢከራይ፣ ግማሽ ሰቀል ብር ለአንድ ወር ይከፍላል።
  • 152፦ ማንም ፈረስ፣ በቅሎ ወይም አህያን ቢከራይ፣ አንድ ሰቀል ብር ለአንድ ወር ይከፍላል።
  • 157፦ የነሐስ መጥረቢያ ክብደት 1.54 ኪሎግራም ቢሆን፣ ኪራዩ አንድ ሰቀል ብር ለአንድ ወር ይሆናል። የመዳብ መጥረቢያ ክብደት 0.77 ኪሎግራም ቢሆን፣ ኪራዩ ግማሽ ሰቀል ብር ለአንድ ወር ይሆናል። የነሐስ [...]-መሣርያ ክብደት 0.5 ኪሎግራም ቢሆን፣ ኪራዩ ግማሽ ሰቀል ብር ለአንድ ወር ይሆናል።
  • 158-ሀ፦ ነጻ ወንድ ነዶ ለማሠር፣ በጋሪ ለመጫን፣ በጎተራ ለማስቀመጥና አውድማን ለመጥረግ እራሱን ለደመወዝ ቢያከራይ፣ ደመወዙ ለሦስት ወር 1500 ሊተር ገብስ ይሆናል። ለ፦ ሴት በመክር ወራት እራስዋን ለደመወዝ ብታከራይ፣ ደመወዝዋ 600 ሊተር ገብስ ለሦስት ወር ሥራ ይሆናል።
  • 159፦ ማንም የበሬዎችን ቡድን ለአንድ ቀን ቢያሠር፣ ኪራዩ 25 ሊተር ገብስ ይሆናል።
  • 160-ሀ፦ አንጥረኛ ክብደቱ 1.5 ሚና የሆነውን የመዳብ ሳጥን ቢሠራ፣ ደመወዙ 5000 ሊተር ገብስ ይሆናል። ለ፦ ክብደቱ 2 ሚና የሆነውን ነሐስ መጥረቢያ ቢሠራ፣ ደመወዙ 50 ሊተር ስንዴ ይሆናል።
  • 161፦ ክብደቱ አንድ ሚና የሆነውን መዳብ መጥረቢያ ቢሠራ፣ ደመወዙ 50 ሊተር ገብስ ይሆናል።
  • 162-ሀ፦ ማንም መስኖ ቢያዛወር፣ አንድ ሰቀል ብር ይከፍላል። ማንም በስውር ውሃን ከመስኖ ቢወስድ፣ የተ[...] ነው። ከሌላው ሰው ቅርንጫፍ በታች ከሆነው ቦታ ቢወስደው፣ ለመጥቀም የርሱ ነው።
  • 162-ለ፦ ማንም [...] ቢወስድ፣ [...] ማናቸውም [...] ያዘጋጃል፣ [...] ማንም በግ ከመስክ ቢ[...]፣ ካሣው [...] ይሆናል፣ ቆዳውንም ሥጋውንም ይሰጣል።
  • 163፦ የማንም እንስሳ ቢያብድ፣ የንጽሕናም ሥነ ስርዓት ቢያደርግበት፣ ወደ ቤትም መልሶ ቢነዳው፣ ጭቃውንም በጭቃው ክምችት ላይ ካደረገው፣ እሱ ግን ባልደረባውን ካልነገረው፣ ባልደርባው ሳያውቀው የራሱን እንስሶች ወደዚያ ነድቶ ቢሞቱ፣ ካሣ ይሆናል።
  • 164፦ ማንም ነገርን ለመያዝ ወደ ሰው ቤት ቢሄድ፣ ጸብም ጀምሮ ወይም ኅብስቱን ወይም የመስዋዕት ዕቃውን ቢሰብር፣
  • 165፦ እርሱ አንድን በግ፣ አሥር ዳቦዎችን፣ አንድን ደምባጃን የ[...] ጠላ ይሰጣል፤ ቤቱንም ታድሶ ይቀድሳል። አንድ ዓመት ጊዜ እስከሚያልፍ ድረስ ከቤቱ ይርቃል።
  • 166፦ ማንም የራሱን ዘር በሌላ ሰው ዘር ላይ ቢዘራ፣ «አንገቱ በማረሻ ላይ ይደረጋል። ሁለት የበሬ ቡድኖችን በማሠር የአንዱ ቡድን ፊት ወዲህ የሌላውንም ቡድን ፊት ወዲያ ያደርጋሉ። ጥፋተኛውም በሬዎቹም ይገደላሉ፤ እርሻውን መጀመርያው የዘራው ለራሱ ያጭደዋል።» ቀድሞ እንዲህ ይካሄዱ ነበር።
  • 167፦ አሁን ግን አንድ በግ ለሰውዬውና ሁለት በጎች ለበሬዎቹ ይተካሉ። 30 ዳቦዎችና 3 ደምባጃን የ[...] ጠላ ይሰጣል፣ ታድሶም ይቀድሰዋል። እርሻውንም መጀመርያው የዘራው ያጭደዋል።
  • 168፦ ማንም የእርሻ ድንበር ጥሶ ከጎረቤቱ እርሻ አንድ ፈር ቢወስድ፣ የተበደለው ባለ እርሻ በጋራ ድንበራቸው ላይ ጥልቀቱ 0.25 ሜትር የሆነውን ስብጥር ቈርጦ ለራሱ ይወስዳል። ድንበሩን የጣሰው አንድ በግ፣ 10 ዳቦዎችና አንድ ደምባጃን የ[...] ጠላ ይሰጣል፣ እርሻውንም ታድሶ ይቀድሰዋል።
  • 169፦ ማንም እርሻን ገዝቶ ድንበሩን ቢጥስ፣ አንድ ወፍራም ዳቦ ይወስድና ለፀሐይ ጣዖቱ ይሰብርና «አንተ ሚዛኔን ወደ ምድር [...]ኻል» ይላል። እንዲህም ይናገራል፦ «የፀሐይ ጣዖት ሆይ፣ የነፋስ ጣዖት ሆይ፣ ጸብ የለም።»
  • 170፦ ነጻ ሰው እባብ ቢገድል፣ የሌላውን ሰው ስም ቢናገር፣ 40 ሰቀል ብር ይከፍላል። ባርያ ቢሆን፣ እሱ ብቻ ይገደላል።
  • 171፦ እናት የልጇን ልብስ ብትወስድ፣ ልጆቿን ከውርስ እየነቀለቻቸው ነው። ልጇ ወደ ቤቷ ቢመልስ፣ በርዋን ወስዳ ታውጣለች፣ [..]ዋን ወስዳ [...] ታውጣቸዋለች። እንዲህ መልሳ ትወስዳቸዋለች፤ ልጇን ዳግመኛ ልጇን ታደርገዋለች።
  • 172፦ ማንም በረሃብ ዓመት የነጻ ሰውን ሕይወት ቢጠብቅ፣ የዳነው ሰው ለራሱ ምትክ ይሰጣል። ባርያ ቢሆን፣ 10 ሰቀል ብር ይከፍላል።
  • 173-ሀ፦ ማንም የንጉሡን ብያኔ ባይቀበለው፣ ቤቱ የፍርስራሽ ክምር ይሆናል። ማንም የአገር ሹም ብያኔ ባይቀበል፣ ራሱን ይቆርጣሉ።
  • 173-ለ፦ ባርያ ከጌታው ቢያምጽ፣ ወደ ሸክላ ጋን ውስጥ ይገባል።
  • 174፦ ሰዎች እርስ በርስ እየመቱ አንዱ ቢሞት፣ ሌላው አንድ ባርያ ይሰጣል።
  • 175፦ ወይም እረኛ ወይም ካቦ ነጻ ሴትን በጋብቻ ቢወስድ፣ ወይም ከ2 ወይም ከ4 ዓመት በኋላ ባርያ ትሆናለች። ልጆቿን [...] ያደርጋሉ፣ ቀብቶቻቸውን ግን ማንም አይዝም።
  • 176-ሀ፦ ማንም በሬ ከበረት ውጭ ቢጠብቀው፣ ለንጉሡ ችሎት ጉዳይ ይሆናል። በሬውን ይሸጣሉ። በሬ በሦስተኛው ዓመቱ ማርባት የሚችል እንስሳ ነው። የማረሻ በሬ፣ አውራ በግና ወጠጤ ፍየል በሦስተኛው ዓመታቸው ማርባት የሚችሉ እንስሶች ናቸው። ለ፦ ማንም የተሠለጠነ ባለ እጅ ቢገዛ፣ ወይም ሸክላ ሠሪ፣ አንጥረኛ፣ አናጢ፣ ቆዳ ፋቂ፣ ሱፍ አጣሪ፣ ሸማኝ ወይም የካልሲ ሠሪ ቢሆን፣ 10 ሰቀል ብር ይከፍላል።
  • 177፦ ማንም እንደ ንግርተኛ የተሠለጠነውን ሰው ቢገዛ፣ 25 ሰቀል ብር ይከፍላል። ማንም ያልተሠለጠነ ሰው ቢገዛ፣ 20 ሰቀል ብር ይከፍላል።
  • 178፦ የማረሻ በሬ ዋጋ 12 ሰቀል ብር ነው። የበሬ ዋጋ 10 ሰቀል ብር ነው። ያደገች ላም ዋጋ 7 ሰቀል ብር ነው። የአጎሬሳ ማረሻ በሬ ወይም ላም ዋጋ 5 ሰቀል ብር ነው። ጡት የጣለ ጥጃ ዋጋ 4 ሰቀል ብር ነው። ላም በጥጃ እርጉዝ ብትሆን ዋጋው 8 ሰቀል ብር ነው። የአንድ ጥጃ ዋጋ 2 ሰቀል ብር ነው። የአንድ ድንጉላ፣ ባዝማ፣ ጭነት አህያ ወይም ሴት አህያ ዋጋ እንዲህ ነው።
  • 179፦ በግ ቢሆን፣ ዋጋው 1 ሰቀል ብር ነው። የ3 ፍየል ዋጋ 2 ሰቀል ብር ነው። የሁለት ጠቦት ዋጋ 1 ሰቀል ብር ነው። የ2 ፍየል ጠቦት ዋጋ ግማሽ ሰቀል ብር ነው።
  • 180፦ የአገሣሥ ፈረስ ቢሆን፣ ዋጋው 20 ሰቀል ብር ነው። የበቅሎ ዋጋ 40 ሰቀል ብር ነው። የተጋጠ ፈረስ ዋጋ 14 ሰቀል ብር ነው። የአጎሬሳ ፈረስ ዋጋ 10 ሰቀል ብር ነው። የሴት አጎሬሳ ፈረስ ዋጋ 15 ሰቀል ብር ነው።
  • 181፦ ጡት የጣለ ወይም የጣለች የፈረስ ግልገል ዋጋ 4 ሰቀል ብር ነው። የ4 ሚና መዳብ ዋጋ 1 ሰቀል ብር ነው፣ 1 ብርሌ ረቂቅ ዘይት 2 ሰቀል ብር ነው፣ አንድ ብርሌ ጮማ አንድ ሰቀል ብር ነው፣ አንድ ብርሌ ቅቤ አንድ ሰቀል ብር ነው፣ አንድ ብርሌ ማር አንድ ሰቀል ብር ነው፣ ሁለት አይቦች አንድ ሰቀል ብር ነው፣ ሦስት ሬኔቶች አንድ ሰቀል ብር ነው።
  • 182፦ የ[...] ልብስ ዋጋ 12 ሰቀል ብር ነው። የረቂቅ ልብስ ዋጋ 30 ሰቀል ብር ነው። ሰማያዊ የሱፍ ልብስ ዋጋ 20 ሰቀል ብር ነው። የ[...] ልብስ ዋጋ 10 ሰቀል ብር ነው። የቡትቶ ልብስ ዋጋ 3 ሰቀል ብር ነው። የ[...] ልብስ ዋጋ 4 ሰቀል ብር ነው። የማቅ ልብስ ዋጋ 1 ሰቀል ብር ነው። የስስ እጀ ጠባብ ዋጋ 3 ሰቀል ብር ነው። የተራ እጀ ጠባብ ዋጋ [...] ሰቀል ብር ነው። ክብደቱ 7 ሚና የሆነው የጨርቅ ጥቅል ዋጋ [...] ሰቀል ብር ነው። የአንድ ትልቅ ተልባ እግር ጨርቅ ጥቅል ዋጋ አምስት ሰቀል ብር ነው።
  • 183፦ የ150 ሊተር ስንዴ ዋጋ 1 ሰቀል ብር ነው። የ200 ሊተር ገብስ ዋጋ ግማሽ ሰቀል ብር ነው። የሀምሳ ሊተር ወይን ጠጅ ዋጋ ግማሽ ሰቀል ብር ነው፣ የሀምሳ ሊተር [...] ዋጋ [...] ሰቀል ብር ነው። የ3600 ካሬ ሜትር በመስኖ የጠጣ እርሻ ዋጋ 3 ሰቀል ብር ነው። የ3600 ካሬ ሜትር የ[...] እርሻ ዋጋ 2 ሰቀል ብር ነው። በአጠገቡ ያለው እርሻ ዋጋ 1 ሰቀል ብር ነው።
  • 184፦ ይህ ቀረጡ ነው፣ እንደ ነበር [...] ነበር በከተማው [...]
  • 185፦ የ3600 ካሬ ሜትር ወይን ሐረግ ቦታ ዋጋ 40 ሰቀል ብር ነው። የታደገ በሬ ቆዳ ዋጋ 1 ሰቀል ብር ነው። የ5 ጥጃዎች ቆዳ ዋጋ አንድ ሰቀል ነው፣ የ10 በሬ ቆዳዎች 40 ሰቀል ብር ነው፣ የጎፍላ በግ ለምድ አንድ ሰቀል ብር ነው፣ 10 የወጣት በግ ለምድ አንድ ሰቀል ብር ነው፣ 4 የፍየል ለምድ 1 ሰቀል ብር፣ 15 የተሸለተ ፍየል ለምድ አንድ ሰቀል ብር ነው፣ 20 የጠቦት ለምድ አንድ ሰቀል ብር ነው፣ 20 የፍየል ጠቦት ለምድ 1 ሰቀል ብር ነው። 2 የታደጉትን በሬዎች ሥጋ የሚገዛ አንድ በግ ይሰጣል።
  • 186፦ ማንም የ2 አጎሬሳ በሬዎች ሥጋ የሚገዛ አንድ በግ ይሰጣል። ማንም 5 ጡት የጣሉ ጥጃዎች ሥጋ የሚገዛ አንድ በግ ይሰጣል። ማንም የ10 ጥጃዎች ሥጋ የሚገዛ አንድ በግ ይሰጣል። ማንም የ10 በጎች ሥጋ የሚገዛ አንድ በግ ይሰጣል። ማንም የ20 በግ ጠቦቶች ሥጋ የሚገዛ አንድ በግ ይሰጣል። ማንም የ20 ፍየሎች ሥጋ ቢገዛ አንድ በግ ይሰጣል።
  • 187፦ ማንም ከላም ጋር ቢተኛ፣ ያልተፈቀደ ጥንድ ነው፤ ይገደላል። ወደ ንጉሥ ችሎት ይመሩታል። ንጉሡ ወይም ቢያስገድሉት፣ ወይም ይቅርታ ቢሰጡት፣ በንጉሡ ፊት አይቀርብም።
  • 188፦ ማንም ከበግ ጋር ቢተኛ፣ ያልተፈቀደ ጥንድ ነው፤ ይገደላል። ወደ ንጉሥ ችሎት ይመሩታል። ንጉሡ ሊያስገድሉት፣ ወይም ይቅርታ ሊሰጡት ይችላሉ። በንጉሡ ፊት ግን አይቀርብም።
  • 189፦ ማንም ከራሱ እናት ጋር ቢተኛ፣ ያልተፈቀደ ጥንድ ነው። ማንም ከሴት ልጁ ጋር ቢተኛ፣ ያልተፈቀደ ጥንድ ነው። ማንም ከወንድ ልጁ ጋር ቢተኛ፣ ያልተፈቀደ ጥንድ ነው።
  • 190፦ ከሞተ ወንድ ወይም ሴት ጋር [...] ቢያደርጉ፣ ጥፋት አይደለም። ወንድ ከእንጀራ እናቱ ጋር ቢተኛ፣ ጥፋት አይደለም። አባቱ ግን ገና ቢኖር፣ ያልተፈቀደ ጥንድ ነው።
  • 191፦ ነጻ ወንድ አንድ እናት ካለቻቸው ነጻ እህቶች ጋርና ከእናታቸው ጋር ቢተኛ፣ አንዲቱ በአንድ አገርና ሌላይቱ በሌላ ቦታ ሲሆኑ፣ ጥፋት አይደለም። በአንድ ቦታ ቢሆን፣ ሴቶቹም እንደ ተዛመዱ ቢያውቀው፣ ያልተፈቀደ ጥንድ ነው።
  • 192፦ የወንድ ሚስት ብትሞት፣ እህቷን ማግባት ይችላል። ጥፋት አይደለም።
  • 193፦ ወንድ ሚስት ካለው፣ ቢሞትም፣ ወንድሙ ባልቴቱን እንደ ሚስቱ ያግባታል። ከሌለ፣ አባቱ ያግባታል። በኋላ አባቱ ሲሞት፣ የርሱ ወንድም የነበረችውን ሚስት ያግባል።
  • 194፦ ነጻ ወንድ አንድ እናት ካለቻቸው ባርያ እህቶች ጋርና ከእናታቸው ጋር ቢተኛ፣ ጥፋት አይደለም። ወንድሞች ከነጻ ሴት ጋር ቢተኙ ጥፋት አይደለም። አባትና ወንድ ልጅ ከአንድ ሴት ባርያ ወይም ሸርሙጣ ጋር ቢተኙ ጥፋት አይደለም።
  • 195-ሀ፦ ወንድ ወንድሙ በሕይወት ሳለ ከወንድሙ ሚስት ጋር ቢተኛ፣ ያልተፈቀደ ጥንድ ነው። ለ፦ ነጻ ወንድ ነጻ ሴትን አግብቶ ወደ ሴት ልጇ ቢቀርብ፣ ያልተፈቀደ ጥንድ ነው። ሐ፦ አንዲቱን ሴት ልጅ አግብቶ ወደ እናትዋ ወይም እህትዋ ቢቀርብ፣ ያልተፈቀደ ጥንድ ነው።
  • 196፦ የማንም ወንድና ሴት ባርዮች ወዳልተፈቀዱ ጥንዶች ቢገቡ፣ ወደ ሌላ ቦታ ያዛውሩዋቸዋል፤ አንዱን በአንዱ ከተማና ሌላውን በሌላ ያሰፍሩዋቸዋል። በአንዱም ፈንታ በግና በሌላውም ፈንታ በግ ይሠዋሉ።
  • 197፦ ወንድ ሴትን በተራሮቹ ቢይዛት፣ የወንዱ ጥፋት ነው፤ በቤትዋ ቢይዛት ግን የሴትዮዋ ጥፋት ነው፤ ሴትዮዋ ትሞታለች። የሴትዮዋ ባል በድርጊቱ ቢያገኛቸው፣ ያለ ወንጀል ሊገድላቸው ይችላል።
  • 198፦ ወደ ቤተ መንግሥት በር ቢያምጣቸውና «ሚስቴ አትሞትም» ቢል፣ የሚስቱን ሕይወት ማዳን ይችላል፤ ግን ጣውንቱንም ደግሞ ማዳንና ራሱን ማልበስ አለበት። «ሁለታቸው ይሞታሉ» ካለ፣ ሽክርክሩን ያንከባልላሉ። ንጉሡ ሊያስገድሉዋቸው ወይም ይቅርታ ሊሰጡዋቸው ይችላሉ።
  • 199፦ ማንም ከዐሳማ ወይም ከውሻ ጋር ቢተኛ፣ ይሞታል። ወደ ቤተ መንግሥት በር ያምጣዋል። ንጉሡ ሊያስገድሉዋቸው ወይም ይቅርታ ሊሰጡዋቸው ይችላሉ፣ ሰውዬው ግን በንጉሡ ፊት አይቀርብም። በሬ በሰው ላይ ቢዘልል፣ በሬው ይሞታል፤ ሰውዬው አይሞትም። አንድ በግ ስለ ሰውዬው ይተኩና ይገድሉታል። ዐሳማ በሰው ላይ ቢዘልል ጥፋት አይደለም።
  • 200-ሀ፦ ሰው ወይም ከፈረስ ወይም ከበቅሎ ጋር ቢተኛ፣ ጥፋት አይደለም፣ ግን ወደ ንጉሡ አይቀርብም፣ ደግሞ ቄስ አይሆንም። ማንም ከስደተኛ ሴትና ከእናትዋ ጋር ቢተኛ ጥፋት አይደለም።
  • 200-ለ፦ ማንም ልጁን እንደ አናጢ ወይም አንጥረኛ፣ ሸማኝ፣ ወይም ቆዳ ፋቂ ወይም እንደ ሱፍ ጠራጊ ለማሠልጠን ቢሠጥ፣ ለማሠልጠኑ ክፍያ 6 ሰቀል ብር መክፈል አለበት። አስተማሪው ባለሙያ እንዲሆን ካደረገው፣ ተማሪው ለአስተማሪው አንድ ሰው ይሰጣል።

ዋቢ ምንጭ

ለማስተካከል
  NODES
HOME 1
languages 1
Note 1