ባቢሎን (አካድኛ፦ ባቢሊ፣ ዕብራይስጥ፦ ባቤል) በመስጴጦምያ የነበረ ጥንታዊ ከተማ ነው። ስሙ በአካድኛ ከ/ባብ/ (በር) እና /ኢሊ/ (አማልክት) ወይም «የአማልክት በር» ማለት ነበር። በዕብራይስጥ ግን ስሙ «ደባልቋል» እንደ ማለት ይመስላል (ዘፍ. 11:9)። «ባቢሎን» የሚለው አጠራር እንደ ግሪክኛው ነው።

ባቢሎን
(አል-ሒላ)
የአሜሪካ ሠራዊት በታደሠው ባቢሎን ፍርስራሽ ሲደርሱ፣ 1995 ዓ.ም.
ሥፍራ
ባቢሎን is located in መስጴጦምያ
{{{alt}}}
መንግሥት የባቢሎኒያ መንግሥት
ዘመን 2070-547 ዓክልበ.
ዘመናዊ አገር ኢራቅ
ጥንታዊ አገር ባቢሎኒያ

መጀመርያው «ባቢሎን» የደቡብ ሱመር ከተማ የኤሪዱ መጠሪያ ስም እንደ ነበር ይመስላል።[1]ሱመራውያን ነገሥታት ዝርዝር ዘንድ፣ ከማየ አይኅ ቀጥሎ ኤሪዱ የዓለሙ መጀመርያው ከተማ ሲሆን፣ ንጉሡ ኤንመርካር (2450 ዓክልበ. አካባቢ) ታላላቅ ዚጉራቶችን (የቤተ መቅደስ ግንቦች) በኤሪዱ እና በኦሬክ እንዳሠራ ይለናል። ይህም በሌሎች ልማዶች እንደሚተረክ የባቢሎንና የኦሬክ መሥራች ናምሩድ የባቢሎን ግንብን እንደ መሥራቱ ታሪክ ይመስላል።

ከሱመር ጽላቶች እንደምናውቅ፣ የኤሪዱ ግንብ ከተተወ በኋላ፣ የሱመር ዋና ከተማ (ዋና ቤተ መቅደስ የተገኘበት) ወደ ኒፑር ተዛወረ። ከዚያ ዘመን በኋላ የአካድ ንጉሥ ታላቁ ሳርጎን (2070 ዓክልበ. ግድም) አዲስ የዋና መቅደስ ከተማ ወደ ስሜኑ ሠርቶ ማዕረጉን ከኒፑር አንዳዛወረ እናንብባለን። በአንዱ ዜና መዋዕል ዘንድ ሳርጎን «የባቢሎን ጒድጓድ አፈር ቆፍሮ አዲስ ባቢሎን በአካድ ፊት ሠራ»፣ በሌላም «ከጒድጓዱ አፈር ቆፍሮ በአካድ ፊት ከተማ ሠራ፣ ስሙንም 'ባቢሎን' አለው።» ከዚህ መረጃ ሳርጎን የኤሪዱን አፈር ወስዶ አዲሱን ባቢሎን በሥፍራው እንደመሠረተው መገመት እንችላለን። ሳርጎንም እንደ ፊተኛው ኤንመርካር «የአራት ሩቦች ንጉሥ» በመባሉ በሌሎች መንግሥታት ሁሉ በላይ ሆኖ በመላው ዓለም ላይ ይግባኝ ማለት እንደ መጣሉ ነበር።

ሆኖም ይህ የኒፑር ቅድምትነት መተካቱ ለጊዜው በሱመራውያን መካከል ተቃውሞ ያገኝ ነበር። ከአካዳውያን፣ ጉታውያንና ሱመራውያን ገዥነት በኋላ፣ አሞራውያን የተባሉት ብሔር ወርሮ አያሌ ከተማ-ግዛቶች መሠረቱ። ከዚህም መካከል አንዱ ካዛሉ ሲሆን አሞራዊው አለቃ ሱሙ-አቡም በ1807 ዓክልበ. ግድም የባቢሎን ነጻነት ከካዛሉ አዋጀ፤ በዚያን ጊዜ እሱ የባቢሎን መጀመርያ ንጉሥ ሆነ። ከባቢሎን ነገሥታት ሃሙራቢ የሃሙራቢ ሕግ ፍትሕ ስለ መፍጠሩ በተለይ ይታወቃል። የባቢሎን መጀመርያ ውድቅት በ1507 ዓክልበ. (ኡልትራ አጭር አቆጣጠር) በኬጥያውያን ንጉሥ ፩ ሙርሲሊ እጅ ደረሰ። ከዚያ የኬጥያውያን ጓደኞች የነበሩት ካሣውያን ብሔር ባቢሎንን ገዛ፣ የከተማውም ስም በካሣኛ «ካራንዱኒያሽ» ተባለ። እነዚህ ካሣውያን እስከ 1163 ዓክልበ. ድረስ ባቢሎኒያን ገዙ።

ለረጅም ዘመናት አሦር በስሜንና የባቢሎኒያ መንግሥት በደቡብ ለመስጴጦምያ ዋና ተወዳዳሪዎቹ ሆኑ። ከ919 ዓክልበ ጀምሮ አሦር ይበረታ ነበር፤ እስራኤልንና ግብጽን እስከሚያሸንፋቸው ድረስ። ከ634 ዓክልበ. በኋላ ግን አሦር ወድቆ ባቢሎኒያ በናቦፖላሣር ሥር እንደገና ነጻነት አገኘ። ልጁም 2 ናቡከደነጾር ከብሉይ ኪዳን እንደሚታወቅ፣ ኢየሩሳሌምን የይሁዳንም ሕዝብ የማረከው (የባቢሎን ምርኮ) ነቢዩም ዳንኤል የነበየለት ንጉሥ ነው፤ ዳንኤልም የናቡከደነጾር የምስል ሕልም አስተረጎመለት። ይህ የባቢሎኒያ መንግሥት በ547 ዓክልበ. ለፋርስ ንጉሥ ታላቁ ቂሮስ ወደቀ።

በ283 ዓክልበ. በግሪኮች ዘመን (ከታላቁ እስክንድር በኋላ)፣ የባቢሎን ኗሪዎችና መቅደስ ወደ ሴሌውክያ በግድ ተዛወሩ። ከዚህ ጀምሮ ባቢሎን አነስተኛ ሥፍራ ሆነ።

ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች በቀድሞ ክርስቲያኖች መሃል፣ የአረመኔው የሮሜ መንግሥት በሥውር እንደ «ባቢሎን» እንደ ታወቀ ይታሥባል። በዚህ ዘመን ስለ ሮሜ መንግሥት በገሃድ ትዝብት ማድረስ እንደ ወንጀል ተቆጠረና። እንዲሁም «ባቢሎን» በዮሐንስ ራዕይ ይጠቀሳል። ዛሬውም በተገኘው በራስታፋራይ እንቅስቃሴ ደግሞ «ባቢሎን» ሲባል ከንጉሣቸው ያመጹትን መንግሥታትና ሥልጣናት ያመልክታል።

ቂሮስ አይሁዶች ወደ ይሁዳ እንዲመለሱ ቢፈቅድም፣ ብዙ አይሁዶች በባቢሎን አካባቢ ቀሩ፣ እነኚህ ከ370-470 ዓም ያህል የባቢሎኒያ ተልሙድ የተባለውን እምነት ጽሑፍ ፈጠሩ።

1975 ዓም የኢራቅ ገዢ ሳዳም ሁሠይን አዲስ ባቢሎን በፍርስራሹ ላይ ማገንባት ጀመረ። በ1996 ዓም ግን የአሜሪካ ሥራዊት በጦርነት አጠፉት።

ደግሞ ይዩ

ለማስተካከል
  1. ^ "Babylon as a Name for Other Cities..." Archived ጁላይ 30, 2012 at the Wayback Machine p. 25-33. (እንግሊዝኛ)
  NODES
Note 1