የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን

(ከካቶሊክ የተዛወረ)
የሮሜ ቄሳውንት በስዊስ አገር

የካቶሊክ እምነት እውነተኛ መነሻ ታሪክ

ለማስተካከል

በክርስትና ታሪክ ስለ ካቶሊክ መነሻ እና የክርስትና መከፋፈል በስፋት ማወቅ ከፈለጉ ይህንን ጽሑፍ በእርጋታ ያንብቡ!

አውጣኪ፣ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ እና የኬልቄዶን ጉባኤ

በቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገ/አማኑኤል

መግቢያ

ከክርስቶስ ልደት በኋላ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በመካከለኛው ምሥራቅ በተለይ በአንጾኪያና በግብጽ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ያወከና ታላቅ ብጥብጥ የፈጠረ በምሥጢረ ሥላሴ እምነት ላይ የተነሣ የተሳሳተ ትምህርት ነበር፡፡ ይኸውም አርዮስ ከእስክንድርያዊው መምህሩ ከአርጌኒስ በቀሰመው ትምህርት በዘዴ ‹‹ክብር ምስጋና ይግባውና እግዚአብሔር ወልድን ፍጡር ነው፤ አምላክም አይደለም፤›› ለማለት ‹‹ሀሎ አመ ኢሃሎ ወልድ›› (ወልድ ያልነበረበት ጊዜ ነበር) በግሪክኛ፡- ‹‹ኢን ፖቴ ኦቴ ኡክ ኢን›› ብሎ የክሕደት ትምህርት በማስተማሩ መላው የክርስትናው ዓለም ታውኮ ነበር፡፡ ይህ በ325 ዓ.ም. በኒቂያ ጉባኤ አርዮስና ኑፋቄው በመወገዙ ችግሩ መፍትሔ አግኝቶ ነበር፡፡ ከ106 ዓመታት በኋላ ደግሞ ንስጥሮስ ከአንጾኪያ በአገኘው ትምህርት በቊስጥንጥንያ ቤተ ክርስቲያን በምሥጢረ ሥጋዌ እምነት ላይ ስለ ክርስቶስ የተሳሳተ ትምህርት ያስተምር ጀመር፡፡

ይኸውም ንስጥሮስ 1ኛ ክርስቶስ ሁለት አካል ሁለት ባሕርይ አለው፤ 2ኛ/ ክርስቶስ ፍጹም ሰው እንጂ ፍጹም አምላክ አይደለም፤ እንዲሁም 3ኛ/ እመቤታችን ሰውን እንጂ አምላክን አልወለደችም፤ ስለዚህ እመቤታችን ወላዲተ ሰብእ እንጂ ወላዲተ አምላክ ልትባል አይገባትም (ሕስወኬ ትሰመይ ወላዲተ አምላክ፣ በአማን ትሰመይ ወላዲተ ሰብእ) ብሎ በማስተማሩ ይህ ኑፋቄ በ431 ዓ.ም. ላይ በታላቁ መምህር በእስክንድርያው ፓትርያርክ በቅዱስ ቄርሎስ አማካኝነት በኤፌሶን ጉባኤ ተወግዞ ችግሩ ተወግዶ ነበር፡፡ ሆኖም የንስጥሮስ የክህደት እምነት ጨርሶ ሳይጠፋ በዚያው በመካከ ለኛው ምሥራቅ በተለይ በፋርስና በባቢሎን እንዲሁም በኤዴሳ ሲስፋፋ ቆይቷል፡፡ እንዲሁም ንስጥሮሳውያን በኤፌሶንና በቊስጥንጥንያ በብዛት ይገኙ ነበር፡፡

አውጣኪና ትምህርቱ

የንስጥሮስን ትምህርት በጥብቅ ይቃወሙ የነበሩት የግብጽ መነኰሳትና ካህናት ነበሩ፡፡ በቊስጥንጥንያም ቢሆን አያሌ የንስጥሮስ ተቃዋሚዎች ነበሩ፡፡ የንስጥሮስን ትምህርት አጥብቆ ይቃወም የነበረና ለኦርቶዶክስ ሃይማኖት እጅግ ቀናኢ የነበረ አውጣኪ የተባለ በቊስጥንጥንያ የአንድ ትልቅ ገዳም አበምኔት (መምህር) ነበር፡፡ አውጣኪ ‹‹ክርስቶስ ሁለት አካል ሁለት ባሕርይ አለው›› የሚለውን የንስጥሮሳውያንን ትምህርት አጥብቆ በመቃወም እሱ ወደ ተቃራኒው የባሰ ክህደት ውስጥ ገባ፡፡ አውጣኪ በቊስጥንጥንያ ‹‹ክርስቶስ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ብቻ አለው፤›› እያለ ያስተምር ጀመር፡፡ አባባሉ የቅዱስ ቄርሎስን ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት ይመስላል፡፡ አውጣኪ ግን ‹‹አንድ ባሕርይ›› ሲል የክርስቶስን መለኮታዊ ባሕርይ ብቻ ማለቱ ነበር፡፡

በአውጣኪ አባባል ‹‹ሁለቱ ባሕርያት ማለት የሥጋና የመለኮት ባሕርያት በተዋሐዱ ጊዜ የመለኮት ባሕርይ የሥጋን ባሕርይ ውጦታል፤ አጥፍቶታል፡፡ ሥጋና መለኮት ከተዋሐዱ በኋላ በክርስቶስ ላይ የሚታየው የመለኮት ባሕርይ ብቻ ነው፡፡ በክርስቶስ የሥጋ ባሕርይ ተውጦ የመለኮት ባሕርይ ብቻ ነው የሚታየው፤›› ይል ነበር፡፡ ይህ አባባል በእኛም ቤተ ክርስቲያን ማለት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተወገዘ ነው፡፡ አውጣኪ በተጨማሪ ከሥጋዌ በኋላ ክርስቶስ ፍጹም ሰው ነው ለማለት ‹‹ክርስቶስ ዘዕሩይ ምስሌነ በትስብእቱ›› ማለት ‹‹ክርስቶስ በትስብእቱ (በሥጋው) ከእኛ ጋር አንድ ነው›› የሚለውን ኦርቶዶክሳዊ አነጋገር አይቀበልም ነበር፡፡ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት መሠረት ‹‹ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ነው፡፡›› ነገር ግን ፍጹም ሰው ካልሆነና እኛን ወክሎ በመስቀል ላይ በሥጋው መከራን ካልተቀበለ፣ የእኛ የሰዎች ድኅነት አስተማማኝ አይሆንም፡፡ በክርስቶስ የሥጋና የመለኮት ባሕርያት ተዋሕደው በመስቀል ላይ በአንድነት ባሕርዩ በተቀበለው መከራ ድኅነትን አግኝተናል፡፡

‹‹በክርስቶስ የሥጋ ባሕርይ ተውጦ ወይም ጠፍቶ የመለኮት ባሕርይ ብቻ ነው የሚታየው›› የሚለውን የአውጣኪን የኑፋቄ (የክህደት) ትምህርት የሰማው የቊስጥንጥንያ ፓትርያርክ ፍላብያኖስ ወዲያውኑ ደብዳቤ ጽፎ ስሕተቱን በማስረዳት አውጣኪ ከስሕተቱ እንዲታረምና ይህን ትምህርት እንዳያሰራጭ አስጠነ ቀቀው፡፡ አውጣኪ ግን የኑፋቄ ትምህርቱን አላቆመም፡፡ ከዚህ ላይ አንድ ነገር ማስታወስ አለብን፤ ይኸውም አውጣኪ ክሪሳፍዮስ ለተባለው ለንጉሠ ነገሥቱ ለዳግማዊ ቴዎዶስዮስ ኃይለኛ ጠቅላይ ሚኒስትር የንስሓ አባት ስለነበር የልብ-ልብ የተሰማው ይመስላል፡፡ ፓትርያርክ ፍላብያኖስም ይህንን ስለሚያውቅ ይመስላል አውጣኪን በጣም ሊጫነው አልፈለገም፡፡

ሆኖም ኃይለኛ የነበረ የዶሪሊያም ሊቀ ጳጳስ የነበረው አውሳብዮስ አውጣኪን አጥብቆ ስለ ተቃወመውና ስለ ከሰሰው፣ የቊስጥንጥንያው ፓትርያርክ ፍላብያኖስ እንደተለመደው የመላው አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳት ተጠርተው ጉባኤ በማድረግ ፈንታ፣ በእርሱ ስር የሚተዳደሩትን ሃያ ዘጠኝ ጳጳሳትንና ሠላሳ ሦስት የገዳማት አበምኔቶችን ብቻ ሰብስቦ በእርሱ ሰብሳቢነት በ448 ዓ.ም. በቊስጥንጥንያ አህጉራዊ ሲኖዶስ አድርጎ የአውጣኪን የክሕደት ትምህርት መመርመር ጀመረ፡፡ አውጣኪ በጉባኤው ላይ እንዲቀርብ ሁለት ጊዜ ተጠርቶ ለመቅረብ አልፈለገም፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ ሲጠራ ብቻ ቀርቦ ስለ ኑፋቄ ትምህርቱ ሲጠየቅ ግልጽ ያልሆነ የሃይማኖት መግለጫ በጽሑፍ አቀረበ፡፡

መግለጫው ግን ስለተከሰሰበት የክህደት ትምህርት ምንም አይገልጥም፡፡ ሆኖም የዶሪሊያም ጳጳስ አውሳብዮስ ግልጥ አድርጎ ‹‹ክርስቶስ በትስብእቱ ከእኛ ጋር አንድ ነው?›› ብሎ በጠየቀው ጊዜ አውጣኪ አንድ አይደለም በማለት ካደ፡፡ ከክህደቱም እንዲመለስ ቢጠየቅ አሻፈረኝ አለ፡፡ ስለዚህ ጉባኤው አውጣኪን አወገዘው፡፡ ከአበምኔት ሹመቱና ከክህነት ሥልጣኑም ሽሮ ተራ ሰው አደረገው፡፡ የሮሙ ፖፕ ለቊስጥንጥንያው ፓትርያርክ ፍላብያኖስ ‹‹ክርስቶስ ሁለት ባሕርያት አንድ አካል አለው›› የሚል የሃይማኖት ፎርሙላ የያዘ ደብዳቤ ልኮለት ስለነበረ፤ አውጣኪ ይህንንም ነበር እንዲቀበል የተጠየቀው፡፡ ይህ ደግሞ ከንስጥሮስ ኑፋቄ ጋር የተዛመደ ስለነበረ (ይህ አባባል መንፈቀ ንስጥሮሳዊ ይባላል) አውጣኪ አልቀበልም አለ፡፡

ስለዚህ አውጣኪ ‹‹የቅዱስ ቄርሎስን ሃይማኖት ስለመሰ ከርኩ እንጂ አንዳች የሃይማኖት ስሕተት ሳይኖርብኝ ያለ አግባብ ተወገዝኩ፤›› ብሎ ለንጉሠ ነገሥቱ ለዳግማዊ ቴዎዶስዮስ አመለከተ፡፡ እንዲሁም ለሮም ፖፕ ለልዮን ቀዳማዊና ለእስክን ድርያው መንበረ ፓትርያርክ ለዲዮስቆሮስ ለሌሎችም ጳጳሳት ደብዳቤ ላከ፡፡ የቊስጥንጥንያው ፓትርያርክ ፍላብያኖስም በበኩሉ የአውጣኪን ኑፋቄና ጉባኤው ስለ እርሱ የወሰነውን ውሳኔ ለፖፕ ልዮን ላከለት፡፡ ፖፑም የጉባኤውን ውሳኔ በማጽደቅ ምሥጢረ ሥጋዌን የያዘ ደብዳቤ ለፍላብያኖስ በድጋሚ ላከለት፡፡ በደብዳቤውም ውስጥ ክርስቶስ ሁለት ባሕርያትና አንድ አካል እንዳለው በግልጽ አስፍሯል፡፡ ይህም አባባል ከላይ እንደተገለጸው መንፈቀ ንስጥሮሳዊ ነው፡፡

ሁለተኛው የኤፌሶን ሲኖዶስ (449)

አውጣኪ በቊስጥንጥንያ እጅግ የተከበረ ሰው ስለነበረና ብዙም ደጋፊዎች ስለነበሩት የእርሱ በ448 ዓ.ም. ጉባኤ መወገዝ ብዙዎችን አስቆጥቶ ነበር፡፡ እንደውም ያወገዘው ፓትርያርክ ፍላብያኖስ ንስጥሮሳዊ ነው እየተባለ ይወራና ይወቀስ ጀመር፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም የነገሩን ክብደት ተመልክቶ ምናልባትም በአውጣኪ ንስሓ-ልጅ በጠቅላይ ምኒስትሩ ተጽእኖ ይሆናል ዓለም-አቀፍ የአብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳት ሲኖዶስ በኤፌሶን እንዲደረግ ለጳጳሳቱ ሁሉ ጥሪ አስተላለፈ፡፡ ስብሰባውም በነሐሴ ወር 449 ዓ.ም. በኤፌሶን እንዲሆን ተወሰነ፡፡ ባለፉት ሲኖዶሶች እንደተደረገው ሁሉ የእስክንድርያው ፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ ሰብሳቢ እንዲሆን ንጉሠ ነገሥቱ ወሰነ፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ሰብሳቢ በመሆኑ ሃያ ሦስት ከሚሆኑ ከግብጽ ጳጳሳት ጋር ቀደም ብሎ ኤፌሶን ደረሰ፡፡

ፖፕ ልዮን ግን ይህ ስብሰባ እንዲደረግ አልፈለገም ነበር፡፡ እንደውም ለንጉሠ ነገሥቱ ታላቅ እኅት ለብርክልያ ንጉሡ ጉባኤውን እንዳይጠራ እንድታግባባው ጠይቋት ነበር፡፡ ሆኖም ንጉሠ ነገሥቱ በሐሳቡ ጸንቶ ጉባኤውን ስለጠራ ፖፑም ሦስት መልእክተኞች ላከ፡፡ በጉባኤው ላይ አንድ መቶ ሠላሳ አምስት ጳጳሳት ተሰብስበው ነበር፡፡ ምንም እንኳ ጉባኤው ስብሰባውን የጀመረው አንድ ሳምንት ዘግይቶ ቢሆንም የሮሙ ፖፕ እንደራሴዎች በዚህ ጊዜ ሊገኙ አልቻሉም፡፡ የቊስጥንጥንያው ፓትርያርክ ፍላብያኖስም በጉባኤው ላይ እንዲገኝ ተጠርቶ አልመጣም፡፡ የቀረበትንም ምክንያት አልገለጠም፡፡ ምናልባትም በእሱ ሰብሳቢነት የተሰበሰበው አህጉራዊ ሲኖዶስ ያወገዘው የአውጣኪ ጉዳይ እንደገና እንዲታይ በመደረጉ ቅር ብሎት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ይህ ደግሞ አዲስ ነገር አልነበረም፡፡ ከዚህ በፊትም ብዙ መናፍቃን አርዮስም ጭምር መጀመሪያ በአህጉራዊ ሲኖዶሶች ከተወገዙ በኋላ ነበር ጉዳያቸው እንደገና በዓለም-አቀፍ ሲኖዶሶች እንዲታዩ የተደረገው፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ጳጳሳት ተጠብቀው ባይመጡም ፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ የተገኙትን አንድ መቶ ሠላሳ አምስት ጳጳሳት ይዞ በነሐሴ ወር 449 ዓ.ም. ስብሰባውን ጀመረ፡፡ ጉባኤው የተደረገው እንደበፊቱ በኤፌሶን በቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ነበር፡፡ ጉባኤውም እንደተጀመረ አውጣኪ ተጠርቶ ስለተከሰሰበት ጉዳይ መልስ እንዲሰጥ ተጠየቀ፡፡ አውጣኪ በቊስጥንጥንያ ሕዝብ እጅግ የተወደደና የተደነቀ ከመሆኑም በላይ በቃላት የሚጫወት ቅንነት የጐደለው ሰው ነበር፡፡ አውጣኪ በጉባኤው ፊት ቀርቦ በራሱ እጅ የተጻፈና የፈረመበት የእምነት መግለጫ አቀረበ፡፡ መግለጫውም ከመነበቡ በፊት ራሱ እንዲህ ሲል ጮኾ ተናገረ፡- ‹‹ከልጅነቴ ጀምሮ በግልጥ በምነና (በብሕትውና) ለመኖር ነበር የምፈልገው፡፡ ዛሬ በሕዝብ መካከል በመገኘቴ ታላቅ ሐዘን ይሰማኛል፡፡ ሆኖም እምነቴን ለመመስከር ስለሆነ ደስታ ይሰማኛል፡፡ በኒቅያ ጉባኤ የተወሰነውንና አባታችን የእስክንድርያው ፓትርያርክ ቅዱስ ቄርሎስ ያስተማረውን እምነት በትክክል እቀበላለሁ፤›› አለ፡፡ ከዚህ በኋላ የጉባኤው ጸሓፊ የሚከተለውን የአውጣኪ የእምነት መግለጫ ማንበብ ጀመረ፤ መግለጫውም እንዲህ ይላል፡-

‹‹ሁሉን በያዘ፣ የሚታየውንና የማይታየውን በፈጠረ በአንድ አምላክ አምናለሁ፡፡ በመለኮቱ ከአብ ጋር አንድ በሚሆን በአንድ ልጁ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አምናለሁ፤ ለእኛ ለሰዎች ሲል ለድኅነታችን ከሰማይ ወረደ፡፡ ሥጋ ለበሰ፤ ሰውም ሆነ፡፡ ታመመ፤ ሞተ፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ ዳግመኛም በሕያዋንና በሙታን ላይ ለመፍረድ ይመጣል፡፡ እርሱ ያልነበረበት ጊዜ ነበረ የሚሉ፣ ከመወለዱም በፊት አልነበረም፤ ካለምንም ተፈጠረ የሚሉት፣ ከአብ ጋር በባሕርዩ የተለየ ነው የሚሉት፣ የእርሱ ሁለቱ ባሕርያት ተቀላቅለዋል ወይም ተዋውጠዋል የሚሉት፣ እነዚህ ሁሉ በአንዲት ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን የተወገዙ ናቸው፡፡ እኔም የምከተለው እምነት ይህ ነው፡፡ በዚህ እምነት እስካሁን ኖሬአለሁ፤ ወደፊትም እስክሞት ድረስ በዚሁ እኖራለሁ፡፡›› የሚል ነበር፡፡

አውጣኪ ይህንን ለጉባኤው ሲያስረዳ ተከትለዉት የመጡትም መነኰሳት አውጣኪ ያቀረበውና የተናገረው ትክክል መሆኑን ከዚያው በጉባኤው ፊት አረጋገጡ፡፡ ስለዚህ ይህን የሃይማኖት መግለጫ ከአዩና ከሰሙ በኋላ አራት ሊቃነ ጳጳሳት ማለት የኢየሩሳሌሙ፣ የአንጾኪያው፣ የኤፌሶኑና የቂሣርው ዘቀጰዶቅያ አውጣኪ በእምነቱ ኦርቶዶክስ ነው በማለት ለጉባኤው አጽንተው ሲናገሩ ሁሉም አውጣኪ ከተከሰሰበት ኑፋቄ ንጹሕ መሆኑን በአንድ ድምፅ ወሰኑ፡፡ ከተላለፈበትም ውግዘት ፈቱት፡፡ ሥልጣነ ክህነቱንም መልሰውለት ወደ ቀድሞው የሓላፊነት ሥራው እንዲመለስ ውሳኔ አስተላለፉ፡፡ የሁለት ባሕርይን ሐሳብ ይቀበል የነበረው የዶሪሊያም ጳጳስ አውሳብዮስ አውጣኪን በመወንጀል መግለጫ ሲያቀርብ በዚያ የተሰበሰቡት መነኰሳትና ምእመናን በታላቅ ድምፅ ‹‹አውሳብዮስ ይቃጠል! አውሳብዮስ በሕይወቱ ይውደም! ክርስቶስን ለሁለት እንደ ከፈለ እሱም ለሁለት ይከፈል!›› እያሉ ይጮኹ ጀመር፡፡

የቊስጥንጥንያን ፓትርያርክ ፍላብያኖስንና አውጣኪን ያወገዙትን ጳጳሳት የሮሙን ፖፕ ልዮን 1ኛን ጭምር አውጣኪን ያለ አግባብ በማውገዛቸውና ሥልጣናቸውን ያለ አግባብ በመጠቀማቸው ጉባኤው ካወገዛቸው በኋላ፣ የሚከተለውን አጭር መግለጫ አወጣ፡- ‹‹ከኒቅያ እስከ ኤፌሶን አባቶቻችን በጉባኤ ተሰብስበው ከወሰኑት ሃይማኖት ሌላ የሚጨምር፣ የሚቀንስ ወይም የሚያሻሽል ቢኖር የተወገዘ ይሁን፡፡›› ዘግይተው የደረሱት የፖፑ መልእከተኞች ዩልዮስና ሬናቱስ የተባሉት ጳጳሳትና ዲያቆን ሂላሩስ ከፖፑ የተላከውን የሃይማኖት መግለጫ ደብዳቤ እንዲነበብ ጠይቀው ነበር፡፡ ነገር ግን ደብዳቤው ‹‹ክርስቶስ ሁለት ባሕርያት አንድ አካል አለው›› ስለሚልና ይህም ከንስጥሮስ ኑፋቄ ጋር ስለሚመሳሰል ጉባኤው እንዲነበብ አልፈቀደም፡፡ በዚህም ምክንያት የፖፑ መልእከተኞች ተቀይመው ወዲያውኑ በድብቅ ከጉባኤው ወጥተው ወደመጡበት ተመለሱ፡፡ የጉባኤውም ውሳኔ በንጉሠ ነገሥቱ በዳግማዊ ቴዎዶስዮስ ጸደቀ፡፡ የቊስጥንጥንያ ፓትርያርክ ፍላብያኖስ በኤፌሶን 2ኛ ጉባኤ እንደተወገዘ ወዲያውኑ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡

የዚህን ጉባኤ ውሳኔ ሲሰማ የሮሙ ፖፕ ልዮን ቀዳማዊ እጅግ ተናዶ ጉባኤውን ‹‹ጉባኤ ፈያት (የወንበዴዎች ጉባኤ)›› ብሎ ጠራው፡፡ የጉባኤውንም ሊቀ መንበር ቅዱስ ዲዮስቆሮስን አወገዘው፡፡ ከእስክንድርያ ጋር የነበረውንም ግንኙነት ጨርሶ አቋረጠ፡፡ ፖፑ ይህን ሁሉ ያደረገው እሱ የላከው የሃይማኖት ነክ ደብዳቤ በጉባኤው ላይ ስላልተነበበና የእርሱም መልእክተኞች በጉባኤው ላይ በሙሉ ባለመካፈላቸው ነበር፡፡ በተጨማሪም ፖፑ ለንጉሠ ነገሥቱ ለዳግማዊ ቴዎዶስዮስ የኤፌሶኑን ጉባኤ የዲዮስቆሮስ ጉባኤ ብሎ በመጥራት በጉባኤው ላይ ያለውን ቅሬታ ከገለጸ በኋላ፣ ሌላ ዓለም አቀፍ ሲኖዶስ (ጉባኤ) እንዲጠራ ጥብቅ ሐሳብ አቀረበ፡፡ እንዲረዳውም የምዕራቡን ክፍል ገዥ (ንጉሥ) የነበረውን ሣልሳዊ ዋሌንቲኒያኖስን (Valentinianus III) እና ሚስቱን ንግሥት አውዶቅሲያን አጥብቆ ለምኖ ነበር፡፡

እነዚህም ባለሥልጣኖች እያንዳንዳቸው ሐሳቡን በመደገፍ ለንጉሠ ነገሥቱ ለዳግማዊ ቴዎዶስዮስ ደብዳቤ ጽፈው ነበር፡፡ ዳግማዊ ቴዎዶስዮስ ግን ሁለተኛው የኤፌሶን ጉባኤ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላቸው የቅዱሳን አባቶች ጉባኤ መሆኑን ገልጦ በመጻፍ ስለ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ምንም የሚያሳስብ ነገር አለመኖሩን ገልጦ አሳስቧቸዋል፡፡ በተጨማሪም የምዕራቡን ንጉሥና ንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ መክሯቸው ነበር፡፡ ፖፕ ልዮን ግን ሌላ ዓለም-አቀፍ ሲኖዶስ እንዲደረግ ዳግማዊ ቴዎዶስዮስን አጥብቆ መጠየቁን ቀጠለ፡፡ ሆኖም የፖፑ ጥረት ሁሉ ውጤት አላስገኘም፡፡ ምክንያቱም ዳግማዊ ቴዎዶስዮስ ለ2ኛው የኤፌሶን ጉባኤ ታላቅ አክብሮት ስለነበረውና ውሳኔውንም በሚገባ ስላጸደቀው ነበር፡፡

የኬልቄዶን ጉባኤ

ሁለተኛው የኤፌሶን ጉባኤ ከአለፈ ከአንድ ዓመት በኋላ በሐምሌ ወር 450 ዓ.ም. ዳግማዊ ቴዎዶስዮስ በድንገት ከፈረስ ላይ ወድቆ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡ ቴዎዶስዮስ ወራሽ ስላልነበረው ለአልጋው ቅርብ የነበረች ታላቅ እኅቱ ብርክልያ (Pulcheria) ነበረች፡፡ ብርክልያ ግን በድንግልና መንኵሳ ነበር የምትኖረው፡፡ ሆኖም ብርክልያ ለሥልጣን ስለጓጓች ምንኵስናዋን አፍርሳ የሮም መንግሥት የጦር አዛዥ ጄኔራል የነበረውን መርቅያን (Marcianus) አግብታ በነሐሴ ወር 450 ዓ.ም. እሱ ንጉሠ ነገሥት እሷ ንግሥት ሆነው የሮምን ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ማስተዳደር ጀመሩ፡፡ ይህ የብርክልያ ምንኵስናን ማፍረስ በኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ በተለይም በግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ተቀባይነትን አላገኘም ነበር፡፡ የሮሙ ፖፕ ግን ከአዲሶቹ የሮም መንግሥት ንግሥትና ንጉሠ ነገሥት ዘንድ ተወዳጅነትን ለማግኘት ሲል ጋብቻቸውን በማወደስ አጸደቀላቸው፤ ቡራኬውንም ላከላቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ፖፕ ልዮን ከቊስጥንጥንያ ንጉሣዊ ቤተሰብ ጋር ወዳጅነትን መሠረተ፡፡ እንኳን ደስ አላችሁ ብሎም በጻፈው ደብዳቤ መጨረሻ ላይ እሱ የፈለገው ዓለም አቀፍ ሲኖዶስ እንዲሰበሰብ አሳሰበ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በንጉሠ ነገሥቱ በመርቅያንና በፖፕ ልዮን መካከል ብዙ የወዳጅነት ደብዳቤዎች ተጻጽፈዋል፡፡

ንጉሠ ነገሥቱ መርቅያን በሥልጣኑ በ2ኛው በኤፌሶን ጉባኤ የተወገዘው የፍላብያኖስ አስከሬን ፈልሶ በቊስጥንጥንያ በሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ክብር እንዲቀበር አደረገ፡፡ የተጋዙት ጳጳሳትም ከግዞት ወጥተው ወደየሥራቸው እንዲመለሱ አደረገ፡፡ በመሠረቱ በሲኖዶስ የተወገዙት ወደ ቀድሞ ሥራቸው መመለስ የሚችሉት በንጉሥ ትእዛዝ ሳይሆን በጳጳሳት ሲኖዶስ መሆን ስለነበረበት ንጉሡ ያደረገው ሕገ-ወጥ ሥራ ነበር:: ፖፑም የሱ ፍላጎት ስለነበረ ይህንን አልተቃወመም፡፡ በተቃራኒው ንጉሡ የተወገዙት ጳጳሳት ወደየሀገረ ስብከታቸው እንዲመለሱ የፍላብያኖስም አስከሬን ወደ ቊስጥንጥንያ ፈልሶ በክብር እንዲቀበር በማድረጉ ፖፕ ልዮን ለንጉሠ ነገሥቱ ልባዊ ምስጋና አቅርቧል፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ መርቅ ያንና ንግሥቲቱ ብርክልያ 2ኛው የኤፌሶን ሲኖዶስ ባቀረበው የሃይማኖት መግለጫ መሠረት ነፃ ያደረገውን አውጣኪንም ያለ ሲኖዶስ ውሳኔ ወደ ሰሜን ሶርያ እንዲጋዝ አደረጉ፡፡

ፖፕ ልዮን በአሳሰበው መሠረት ንጉሥ መርቅያን ጥቅምት 8 ቀን 451 ዓ.ም. ዓለም-አቀፍ ሲኖዶስ እንዲደረግ ለጳጳሳት ሁሉ ጥሪ አስተላለፈ፡፡ ጉባኤውም እንዲደረግ የታሰበው ከቊስጥንጥንያ 96 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በምትገኝ በኒቅያ ነበር፡፡ ነገር ግን በጸጥታ ምክንያት ከቊስጥንጥንያ 3 ኪሎ ሜትር ብቻ ርቃ በምትገኘው በኬልቄዶን እንዲሆን ንጉሡ ስለ ወሰነ ጉባኤው በኬልቄዶን ሆነ፡፡ ንጉሥ መርቅያንና ንግሥት ብርክልያ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ተገኝተዋል፡፡ ጉባኤው በሥነ ሥርዓት መካሄዱን የሚቆጣጠሩ 18 ዳኞች በንጉሡ ተሠይመው ነበር፡፡ እነዚህ ሁሉ ዳኞች መሠየማቸው መንግሥት ሲኖዶሱን ምን ያህል እንደተቈጣጠረው ያመለክታል፡፡ የጉባኤው አባላት አቀማመጥ እንደሚከተለው ነበር፤

ዳኞቹ በመኻል ከዳኞቹ በስተግራ የፖፑ መልእክተኞች፣ ቀጥሎ የቊስጥንጥንያው አናቶልያስ፣ የአንጾኪያው ማክሲሙስ፣ የቂሣርያውና የኤፌሶኑ ጳጳሳትና ሌሎች የምሥራቅና የመካከለኛው ምሥራቅ አህጉር ጳጳሳት ሲሆኑ፣ በቀኝ በኩል ቅዱስ ዲዮስቆሮስ፣ የኢየሩሳሌም፣ የተሰሎንቄ፣ የቆሮንቶስ፣ የግብጽ፣ የኢሊሪኩም፣ የፍልስጥኤም ጳጳሳትና ሌሎች ጳጳሳት ተቀምጠዋል፡፡ በኤፌሶን ጉባኤ የተወገ ዙትን ንስጥሮሳውያን መናፍቃንን የቂሮስ ኤጲስቆጶስ ቴዎዶሪጦስንና የኤዴሳን ኤጲስቆጶስ ኢባንን የዚህ ጉባኤ አባላት አድርገው ተቀበሏቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ብዙ ብጥብጥ ተነሣ፤ የግብጽ ጳጳሳት በኤፌሶን ጉባኤ የተወገዙትን ንስጥሮሳውያን ቴዎዶሪጦስንና ኢባንን ጉባኤው በአባልነት በመቀበሉ ‹‹አይሁዶችን፣ የክርስቶስን ጠላቶች ከዚህ አስወጡ!›› እያሉ በመጮኽ ተቃውሟቸውን አሰሙ፡፡ ጉባኤው ግን የእነሱን ጩኸት ከቁም ነገር አልቈጠረውም፡፡

ጉባኤውን በሊቀ መንበርነት በተራ የመሩት ከመንግሥት የተሠየሙት ዳኞችና የሮሙ ፖፕ መልእከተኞች ነበሩ፡፡ የሮሙ ተወካዮች ጉባኤውን ሲመሩ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ነበር፡፡ ከአሁኑ በስተቀር ባለፉት ዓለም-አቀፍ ሲኖዶሶች ሁሉ የእስክንድርያው ፓትርያርክ ከሊቃነ መናብርቱ ዋናው ነበር፡፡ አሁን ግን የእስክን ድርያውን ፓትርያርክ ዲዮስቆሮስን ለመኰነን የተሰበሰበ ሲኖዶስ ስለሆነ ዲዮስቆሮስ ከሊቃነ መናብርቱ አንዱ አልሆነም፡፡ የጉባኤው አባላት ቦታቸውን ይዘው እንደተቀመጡ የሮሙ ፖፕ ተወካይ ፓስካሲኑስ (Paschasinus) ተነሥቶ ለዳኞቹ ፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ ከተቀመጠበት ቦታ ማለት ከጉባኤው እንዲነሣና ሌላ ቦታ እንዲቀመጥ አመለከተ፡፡ የመንግሥቱ ዳኞች ለምን ይነሣል ብለው በጠየቁ ጊዜ፣ ሌላው የፖፑ መልእክተኛ ሊሴንቲያስ (Licentius) የተባለው ዲዮስቆሮስ ከዚህ በፊት የሮሙ ፖፕ ሳይፈቅድ በሥልጣኑ ሲኖዶስ (የ449 ሲኖዶስን ማለቱ ነው) እንዲካሄድ አድርጓል በማለት ክስ አቀረበ፡፡

ይህ ግን መሠረት የሌለው ክስ ነበር፡፡ ምክንያቱም ከዚህ በፊት የተደረጉት ሲኖዶሶች ሁሉ የተጠሩትና የተካሄዱት በሮም ንጉሠ ነገሥት ፈቃድና ትእዛዝ እንጂ በሮሙ ፖፕ ፈቃድ አልነበረም፡፡ ያለፈውም የሁለተኛው የኤፌሶን ሲኖዶስ የተጠራው በዳግማዊ ቴዎዶስዮስ ትእዛዝ እንጂ በፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ ሥልጣን አልነበረም፡፡ ስለዚህ የቀረበው ክስ ዳኞቹን አላረካ ቸውም፡፡ በዚህ ጉዳይ ብዙ ጭቅጭቅ ስለተፈጠረ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ በፈቃዱ ቦታውን ለቆ ተከሳሾች በሚቀመጡበት ቦታ ሄዶ ተቀመጠ፡፡ የሮሙ ፖፕ ተወካዮች በሁለተኛው የኤፌሶን ጉባኤ ፓትር ያርክ ዲዮስቆሮስ የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና አፍርሷል ሲሉ ከሰሱ፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ሲመልስ እሱ በንጉሠ ነገሥቱ በቴዎ ዶስዮስ ትእዛዝና ጥያቄ መሠረት ነው ጉባኤውን የመራው፡፡ እሱ ቀኖናን አፈረሰ? ወይስ በኤፌሶን ጉባኤ የተወገዙትን ንስጥሮሳውያን መናፍቃንን የቂሮስ ኤጲስ ቆጶስ ቴዎዶሪጦስንና የኤዴሳን ኤጲስቆጶስ ኢባንን የዚህ ጉባኤ አባላት አድርገው የተቀበሉት እነሱ ናቸው ቀኖና አፍራሾች? ብሎ ጥያቄ አቀረበ፡፡ ሆኖም ይህ የፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ ጥያቄ ምንም መልስ ሳይሰጠው በዝምታ ታለፈ፡፡

ቀጥሎ በ2ኛው የኤፌሶን ጉባኤ የተወገዘው የዶሪሌኡም ኤጲስቀጶስ አውሳብዮስ ተነሥቶ ዲዮስቆሮስ እሱንና የቊስጥንጥንያውን ፍላብያኖስን ‹‹ምንም የሃይማኖት ጕድለት ሳይገኝብን ያለ አግባብ አውግዞናል ጥቃትም አድርሶብናል፡፡ በተጨማሪም አውጣኪን ከግዝቱ በመፍታት የኦርቶዶክስ እምነትን አበላሽቷል፤›› በማለት ክስ አቀረበ፡፡ ይህ ተመሳሳይ ክስ በሮሙ ፖፕ ተወካዮችም ቀርቧል፡፡ በመሠረቱ ይህ ክስ እውነት እንኳ ቢሆን የሚመለከተው ሲኖዶሱን እንጂ የሲኖዶሱን ሊቀ መንበር ዲዮስቆሮስን አልነበረም፡፡ ከዚህ ላይ ልንገነዘበው የሚገባው የሮሙ ፖፕ ተወካዮችም ሆኑ ከሳሹ አውሳብዮስ በአጠቃላይ የኬልቄዶን ጉባኤም ቢሆን ዲዮስቆሮስን በእምነት ክህደት አልከሰሱትም፡፡ ሆኖም መናፍቅ ነው ተብሎ የታሰበውን አውጣኪን የ449 ዓ.ም. ሲኖዶስ ነጻ አድርጎ ከውግዘቱ ስለፈታው ብቻ ዲዮስቆሮስን የአውጣኪን የኑፋቄ ትምህርት ተቀብሏል ብለው በጭፍኑ ደምድመዋል፡፡ አውጣኪ ግን በፊት ያስተምር የነበረውን የኑፋቄ ትምህርት ትቶ በቃልም በጽሑፍም ኦርቶዶክሳዊ የእምነት መግለጫ በማቅረቡ በዚህ መሠረት ነው 2ኛው የኤፌሶን (የ449) ሲኖዶስ ነጻ ያደረገው፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ አውጣኪ ያቀረበው የእምነት መግለጫ የሚገኝበት የ449 ሲኖዶስ ቃለ ጉባኤ እንዲነበብ ጠየቀ፡፡

የ449 ሲኖዶስ ቃለ ጉባኤ የመጀመሪያው ክፍል ከተነበበ በኋላ ጉባኤውን የጠራው ንጉሡ ዳግማዊ ቴዎዶስዮስ መሆኑና አውጣኪንም ነጻ ያደረጉት በጉባኤው የነበሩት ጳጳሳት በሙሉ ተስማምተው በፊርማቸው ያጸደቁት መሆኑ ተነበበ፡፡ በ449 ዓ.ም. በ2ኛው የኤፌሶን ሲኖዶስ ላይ የነበሩት ጳጳሳት ግን የ449 ሲኖዶስን ውሳኔ ፈጽሞ እንደማያውቁት የፈረሙትም በወታደሮች ተገደው በባዶ ወረቀት ላይ መሆኑን አጥብቀው ተናገሩ:: የግብጽ ጳጳሳት ግን ይህን በሰሙ ጊዜ ‹‹የክርስቶስ ወታደር የዚህን ዓለም ባለሥልጣን ፈጽሞ አይፈራም፡፡ እሳት አንድዱ አንድ ሰማዕት እንዴት እንደሚሞት እናሳያችሁ!›› ብለው በጉባኤው ፊት ተናገሩ፡፡ ባዶ ወረቀት ላይ ነው የፈረምነው ካሉት አንዱ የኤፌሶኑ ኤጲስ ቆጶስ እስጢፋኖስ ነበር፡፡ ይህ ሰው አውጣኪ ነጻ እንዲደረግ ተነሥተው ከተናገሩት ሰዎች ሁለተኛው ነበር፡፡ አውሳብዮስና ፍላብያኖስም እንዲወገዙ ከተናገሩት 5ኛው ተናጋሪ እሱ ነበር፡፡ የሲኖዶሱ ጸሓፊ በ449 ሲኖዶስ ቃለ ጉባኤ ላይ የአውጣኪን የሃይማኖት መግለጫ ሲያነብ አንዳንድ አባቶች ይህን መግለጫ እንዳላዩትና ፊርማቸውም አስመስሎ የተፈረመ ነው በማለት ካዱ፡፡

ከዚህ በኋላ በጉባኤው ፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ እምነቱን እንዲገልጽ ተጠይቆ ሁለቱ ባሕርያት (የመለኮትና የሥጋ) ያለ መቀላቀልና ያለ ትድምርት፣ ያለ መለወጥና ያለ መለያየት በአንድ አካል እንደተዋሐዱ በሚገባ አስረዳ፡፡ እንዲሁም በቅዱስ ቄርሎስ ትምህርት መሠረት ‹‹አአምን በአሐዱ ባሕርይ (ህላዌ) ዘቃለ እግዚአብሔር ሥግው፤›› ብሎ አስረዳ፡፡ ጉባኤውም በዚህ በዲዮስቆሮስ እምነት ላይ ምንም እንከን፣ ምንም ስሕተት አላገኘም፡፡ ጉባኤው በሌላ መንገድ ‹‹አውጣኪ በጽሑፍ ካቀረበው የተለየ በቃል ቢናገር ምን ትፈርድ ነበር?›› ብለው በጠየቁት ጊዜ፣ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ‹‹አውጣኪ የጻፈውን ትቶ ሌላ የክህደት ነገር ቢናገር፣ እሱን ማውገዝ ብቻ ሳይሆን በእሳትም እንዲቃጠል እፈርድበት ነበር፤›› ብሎ መለሰ፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ በእንደዚህ ያለ ነጐድጓዳዊ አነጋገር ሁሉን ግልጥልጥ አድርጎ በተናገረ ጊዜ፣ ኬልቄዶናውያን ጸጥ አሉ፡፡ ዲዮስቆሮስን በመቃወም የተናገሩ የምሥራቅ አህጉር ጳጳሳት ግን ንግግሩ ልባቸውን ነክቶት ‹‹በድለናል፤ ይቅርታ እንጠይቃለን!›› በማለት ጮኹ፡፡

የመንግሥቱ ዳኞች በባዶ ወረቀት ላይ ነው የፈረምነው ስላሉት እንደገና ሲጠይቋቸው ‹‹በድለናል፤ ይቅርታ እንጠይቃለን፤›› ሲሉ መለሱ፡፡ እንደገና ፍላብያኖስን ዲዮስቆሮስ ነው ያስገደለው ስላሉት ቢጠየቁ አሁንም ‹‹በድለናል፤ ይቅርታ እንጠይቃለን፤›› ሲሉ መለሱ፡፡ በዚህ ሁኔታ እነዚህ ጳጳሳት 1ኛ/ በሐሰት በባዶ ወረቀት ላይ ፈርመናል በማለታቸውና፣ 2ኛ/ ፍላብያኖስንና አውሳብዮስን ያለ አግባብ በማውገዛቸው ይቅርታ ጠየቁ፡፡ የመንግሥቱ ዳኞች ፍላብያኖስ ኦርቶዶክስ መሆኑን አጥብቀው በጠየቁ ጊዜ፣ የሮሙ ተወካዮችና አብዛኞቹ አባላት በ449 ሲኖዶስ ጊዜ የነበሩትም ጭምር ፍላብያኖስ ኦርቶዶክስ እንደነበረ ተናገሩ፤ ‹‹ታዲያ ለምን ተወገዘ?›› ሲሉ ዳኞቹ ጠየቁ፡፡ በዚህ ጊዜ ዲዮስቆሮስ ፍላብያኖስ ‹‹ክርስቶስ ከሥጋዌ በኋላ ሁለት ባሕርያት እንዳለው አጥብቆ ይናገር ነበር፤›› ብሎ ተናገረ፡፡ የዚህም እውነት እንዲወጣ ብሎ የ449 ሲኖዶስ ቃለ ጉባኤ ቀርቦ እንዲነበብ አበክሮ ጠየቀ፡፡ ለዚህ ምንም መልስ አልተሰጠውም፡፡

ሁሉም ዳኞቹም ጭምር ቃለ ጉባኤው እንዳይነበብ ስለፈለጉ ጸጥ አሉ፡፡ ሁሉም ዝም ቢሉም ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ንግግሩን በመቀጠል ፍላብያኖስ ‹‹ክርስቶስ ከሥጋዌ በኋላ ሁለት ባሕርያት አለው፤›› እያለ እንደሚናገር መልሶ መላልሶ አስረዳ፡፡ የቀድሞ አባቶች ግን ለምሳሌ አትናቴዎስ፣ ጎርጎርዮስና ቄርሎስ ‹‹አሐዱ ባሕርይ ዘእግዚአብሔር ቃል ሥግው›› እንጂ ከተዋሕዶ በኋላ ‹‹ሁለት ባሕርያት›› ፈጽሞ እንደማይሉ በመጻሕፍቶቻቸው ሁሉ ለማንበብ እንደሚቻል አስረዳ፡፡ የቀረቡትን ማስረጃዎች ሁሉ ከቁም ነገር ሳያስገቡ ጉባኤውም በሚገባ ሳይወያይበት ዳኞቹ በጭፍን ፍላብያኖስና አውሳብዮስ ያላግባብ ነው የተወገዙት በማለት ውሳኔ አሳለፉ፡፡ በተጨማሪም አውጣኪ ቀርቦ ሳይጠየቅ ለ449 ጉባኤ ያቀረበውንም የሃይማኖት መግለጫ ሳይመለከቱ፣ በጭፍን በ449 ሲኖዶስ ላይ ያለ አግባብ ነው ነጻ ሆኖ ከግዝቱ የተፈታው ብለው ዳኞቹ፣ የፖፑ ተወካዮችና ሌሎቹ የጉባኤው አባላት ወሰኑ፡፡ ይህ በግልጥ የሚያመለክተው የኬልቄዶን ጉባኤ የተጠራው ዲዮስቆሮስንና አውጣኪን ለማውገዝና ፍላብያኖስንና አውሳብዮስን ነጻ ለማድረግ መሆኑን ነው፡፡

ከላይ ለቀረቡት ጥብቅ ማስረጃዎች ምንም መልስ ሳይሰጡ የመንግሥቱ ዳኞችና የሮሙ ፖፕ እንደራሴዎች የፖፑን የዶግማ ደብዳቤ (Tomos) አስተያየቱን እንዲገልጥ ለፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ ሰጡት፡፡ ዲዮስቆሮስም ለጥቂት ጊዜ ከአነበበው በኋላ፣ ደብዳቤው ኦርቶዶክሳዊ ሳይሆን ንስጥሮሳዊ መሆኑን ገልጦ ደብዳቤውንና ደራሲውን ያለ አንዳች ማመንታት አወገዘ፡፡ ከተሰበሰቡት ጳጳሳት ብዙዎቹ ስለ ልዮን ደብዳቤ (Tomos) የዲዮስቆሮስን አስተያየትና ስሜት ተጋርተዋል፡፡ ነገር ግን አስተያታቸውን በይፋ ለመግለጥ ድፍረት አልነበራቸውም፡፡ ሌሎች ደግሞ ስለዚሁ ደብዳቤ ታላቅ ጥርጣሬና መደናበር እንዳደረባቸው በፊታቸው ላይ ይነበብ ነበር፡፡ ይህን የአባላቱን ሁኔታ የተመለ ከቱት ዳኞች በደብዳቤው ውስጥ የሚያውክና የሚያስቸግር ነገር እንዳለ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ አንዳንድ ጳጳሳት ምንም ችግር አለመኖሩን ገልጠው፣ ሆኖም አንዳንድ የላቲን ቃላትንና አባባሎችን በደንብ ለመመርመር ጊዜ ለማግኘት ስብሰባው ለአምስት ቀናት እንዲበተን ጠየቁ፡፡ ጥያቄአቸውም ወዲያውኑ ተቀባይነት አግኝቶ ስብሰባው ተበተነ፡፡

ነገር ግን ከሦስት ቀናት በኋላ ጳጳሳቱ የመንግሥቱ ዳኞች በሌሉበት ለነሱም ሳይነግሩ ይፋዊ ስብሰባቸውን በፖፑ እንደራሴ ፓስካሲኑስ (Paschasinus) ሊቀ መንበርነት ቀጠሉ፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ የግብጽ ጳጳሳትና ሌሎች ብዙ ጳጳሳት አልተገኙም፡፡ ስብሰባውን እንደጀመሩ የፖፑ እንደራሴና የስብሰባው ሊቀ መንበር ‹‹የፖፑ ደብዳቤ መከበር አለበት፡፡ ሁሉም ደብዳቤውን መቀበል አለባቸው፡፡ ይህን ደብዳቤ የሚቃወም ተከሶ በጉባኤው ፊት መቅረብ አለበት፤›› ሲል አወጀ፡፡ ወዲያውኑ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ወደ ስብሰባው እንዲመጣ ወደ ማረፊያ ቦታው ሦስት ጳጳሳትና አንድ ዲያቆን ተላኩ፡፡ በዚያን ጊዜ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ከቤት እንዳይወጣ ንግሥት ብርክልያ ባዘዘቻቸው ወታደሮች ይጠበቅ ነበር፡፡ መልእክተኞቹም ዲዮስቆሮስን ወደ ጉባኤው እንዲመጣ በጠየቁት ጊዜ፣ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ‹‹ጉባኤው የተበተነው ለአምስት ቀናት ሲሆን አሁን ገና ሦስት ቀናት ነው ያለፉት፡፡ አሁን እንዴት ለመሰብሰብ እንችላለን? ለመሆኑ የመንግሥቱ ተወካዮች ዳኞች ተነግሯቸዋል?›› ብሎ ጠየቀ፡፡ ለመጀመሪያው ጥያቄ መልስ አልተሰጠውም፡፡ ለሁለተኛው ጥያቄ ግን ‹‹ለቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ምእመናን አያስፈልጉም፤›› ሲሉ መለሱለት፡፡

ቀጥሎ ከቤት ወጥቶ ወደ ስብሰባው ለመሄድ ይፈቅዱለት እንደሆነ ወታደሮቹን ማስፈቀዳቸውን መልእክተኞቹን ጠየቀ፡፡ እነርሱም በበኩላቸው ‹‹እኛ የተላክነው አንተን እንድንጠራ ነው እንጂ ወታደሮችን እንድንጠይቅ እይደለም፤›› ሲሉ መለሱና ተመልሰው ሄዱ፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ሌሎች መልእክተኞች ለዲዮስቆሮስ ሌላ ጥሪ አቀረቡ፡፡ እሱም የመንግሥት ተወካዮች ዳኞች ከሌሉ እንደማይ መጣ ነግሯቸው ተመለሱ፡፡ ይህ ሁሉ የተደረገው በሲኖዶስ ሕግ መሠረት አንድ ሰው ሦስት ጊዜ ተጠርቶ ካልመጣ እንደሚወገዝ ስለሚያውቁ በዚሁ መሠረት ዲዮስቆሮስን በሌለበት ለማውገዝና የፖፕ ልዮንን የዶግማ ደብዳቤ (Tome of Leo) ሁሉም እንዲቀበሉት ለማድረግ ነበር፡፡ ይህም የታቀደው በፖፑ ወኪሎች ነበር፡፡ በዚህ መካከል ሌሎች ከሳሾች ቀርበው በፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ ላይ የተለያዩ እምነትን የማይመለከቱ የሐሰት ክሶችን እንዲያቀርቡ ተደረገ፡፡ በመጨረሻም ዲዮስቆሮስ ወደ ጉባኤው እንዲመጣ ለሦስተኛ ጊዜ መልእክተኞች ላኩበት፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ የኬልቄዶን ጉባኤ ሤራ በደንብ ስለገባው የሃይማኖት መልእክቱን ቀደም አድርጎ ያስተላለፈ መሆኑን ገልጾ በሕመም ምክንያት ወደ ጉባኤው ለመሄድ አለመቻሉን ስለገለጠላቸው መልእክተኞቹ ተመልሰው ሄዱ፡፡ የፖፑ ተወካዮችና አንዳንድ የእነርሱ ደጋፊዎች ዲዮስቆሮስን ለማውገዝ ይህንኑ ነበር የፈለጉት፡፡

የቅዱስ ዲዮስቆሮስ በኬልቄዶናውያን መወገዝ

የሮሙ ፖፕ ልዮን፣ የሮም የምሥራቁ ክፍል ንጉሠ ነገሥት የመርቅያንና የንግሥቲቱ የብርክልያ ታላቅ ተጽእኖ የነበረበት ይህ የኬልቄዶን ጉባኤ መጀመ ሪያም የተሰበሰበው ዲዮስቆሮስን ለማው ገዝና ከሥልጣኑ ለማውረድ ስለነበረ፣ እሱን ለማውገዝ ብዙ ምክንያቶች ይፈልጉ ነበር፡፡ በሃይማኖት በኩል ምንም ስሕተት ስላላገኙበት የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና አፍርሷል በማለት እሱን ወንጀለኛ ለማድረግ አስበው ሕጉን የሚያስከብሩት የመንግሥት ዳኞች ለአምስት ቀናት ጉባኤውን በበተኑበት ጊዜ ከግማሽ ያነሱ አባላት ተሰብስበው ቅዱስ ዲዮስቆሮስ በጉባኤው ላይ እንዲገኝ ሦስት ጊዜ ደጋግመው ጥሪ እንዲደርሰው አደረጉ፡፡ ዲዮስቆሮስም ከላይ እንደተገለጸው ሕግ አስከባሪዎቹ ዳኞችና ሌሎች ከእርሱ ጋር የተከሰሱት በሌሉበት ለመገኘት ስላልፈለገ በጉባኤው ላይ አልተገኘም፡፡ ይህን ምክንያት አድርገው ‹ሲያሻኝ ጭስ ወጋኝ› እንደሚሉት ቀኖና አፍርሷል በማለት የተሰበሰቡት በአንድ ድምፅ አወገዙት፡፡

ሲያወግዙትም ሦስት ምክንያቶች ዘርዝረዋል፤ 1ኛ/ በመናፍቅነት የተከሰሰውንና የተወገዘውን አውጣኪን ነጻ አድርጎ ወደ ቤተ ክርስቲያን አንድነት መልሶታል፡፡ ከዚህ ላይ አውጣኪ በጽሑፍ ያቀረ በውንና በቃልም ያረጋገጠውን ኦርቶዶክሳዊ የሃይማኖት መግለጫ ሊመለከ ቱት አልፈለጉም፡፡ 2ኛ/ የሮሙ ፖፕ ልዮን የላከውን የሃይማኖት መግለጫ ደብዳቤ (The Tome of Leo) ባለመ ቀበል ደብዳቤውንም ፖፕ ልዮንንም አውግዟል የሚል ነው፡፡ 3ኛ/ በጉባኤው ላይ እንዲገኝ ሦስት ጊዜ ተጠርቶ አልተገኘም የሚል ነበር፡፡

ፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ ከተወገዘና ከሥልጣን እንዲወርድ ከተወሰነበት በኋላ ንግሥት ብርክልያ በግል አስጠርታ ሐሳቡን ለውጦ በልዮን ጦማር (Tome of Leo) ላይ እንዲስማማና እንዲፈርም ትእዛዝ አዘል ምክር ሰጥታው ነበር ይባላል፡፡ እሱ ግን መንፈሰ ጠንካራ ስለነበር የንግሥቲቱን ትእዛዝና ምክር አልተቀበለም፡፡ በዚህ ተናዳ ንግሥቲቱ ቅዱስ ዲዮስቆሮስን በወታደሮች በሚያሰቅቅ ሁኔታ አስደበደበችው፡፡ በዚህም ድብደባ ጥርሶቹ ወላልቀው ጽሕሙም ተነጫጭቶ ነበር፡፡ እሱም የተነጨ ጽሕሙንና የወለቁትን ጥርሶች በአንድ ላይ ቋጥሮ ‹‹ይህ የሃይማኖት ፍሬ ነው፤›› የሚል ጽፎበት ለግብጽ ምእመናን ልኮላቸዋል ይባላል፡፡

የቅዱስ ዲዮስቆሮስ ወደ ግዞት መላክ

እጅግ የሚገርመው የኬልቄዶን ጉባኤ ስብሰባውን ሳይፈጽም የጉባኤውም ዘገባ ገና ሳይደርሰው የቊስጥ ንጥንያ ንጉሠ ነገሥት መርቅያን የጉባኤውን ውሳኔዎች ሁሉ የሚያጸድቅ ጽሑፍ ለጉባኤው ላከ፡፡ እንዲሁም ንጉሡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ጋግራ (ጋንግራ) ወደሚባል ደሴት እንዲጋዝ ትእዛዝ አስተላለፈ፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ወደተጋዘበት ወደ ደሴተ ጋግራ በሄደ ጊዜ በፈቃዳቸው ሁለት ጳጳሳትና ሁለት ዲያቆናት ተከትለዉት ሄደው ነበር፡፡ ሦስተኛው ጻድቅ የነበረ መቃርዮስ የተባለ የኤድኮ ጳጳስ አብሮት ለመሄድ በመንገድ ላይ ሳለ ‹‹ቅዱስ ማርቆስ ደሙን ባፈሰሰበት ከተማ የሰማዕትነት አክሊል ስለሚጠብቅህ ቶሎ ብለህ ሂድ እንዳያመልጥህ፤›› ብሎ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ስለነገረው ወዲያውኑ ወደ ግብጽ ሄደ፡፡ ንጉሠ ነገሥት መርቅያን ፓትርያርክ ዲዮስቆሮስን ወደ ግዞት እንዲላክ ከአደረገ በኋላ የጉባኤው ውሳኔ በመንግሥት መጽደ ቁን በመግለጽ ለእስክንድርያና ለመላዋ የግብጽ ሕዝብና ለግብጽ ቤተ ክርስቲያን መልእክት ላከ፡፡ ወዲያውኑም በዲዮስቆሮስ ምትክ ፕሮቴሪዮስ የሚባል ኤጲስ ቆጶስ በቊስጥ ንጥንያ ሹሞ ወደ እስክንድርያ በብዙ ወታደሮች ታጅቦ እንዲሄድ አደረገ፡፡ ወታደሮቹም ለአዲሱ ፓትርያርክ የማይታዘዙትንና የማይገዙትን ከባድ ቅጣት እንዲቀጡ በጥብቅ ታዝዘው ነበር፡፡

የግብጽ ክርስቲያኖች ግን ለዲዮስቆሮስ ታማኝነታቸውን በመግለጥ ንጉሡ ለላከው ፓትርያርክ አንገዛም አሉ፡፡ የግብጽ ጳጳሳትም አስቸኳይ ስብሰባ አድርገው ለፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ ታማኝነታቸውን በአንድ ድምፅ ገልጠው፣ ፖፕ ልዮንንና የልዮንን ጦማር (The Tome of Leo I) እንዲሁም የኬልቄዶንን ጉባኤን ጉባዔ ከለባት ብለው በመጥራት አወገዙት፡፡ ፓትርያርክ አንዲሆን የተላከባቸውንም ፕሮቴሪዮስን አወገዙ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ መርቅያንም ይህን እንደሰማ አጸፋውን ለመመለስ ጳጳሳቱ በሙሉ በኬልቄዶን ጉባኤ ውሳኔና በልዮን ጦማር ላይ እንዲ ፈርሙ በግብጽ ለነበሩት የጦር ሹማም ንቱና መኰንኖቹ ትእዛዝ አስተላለፈ፡፡ መኰንኖቹም በትእዛዙ መሠረት ጽሑፎቹን ለማስፈረም ወደየጳጳሳቱ ሲሄዱ መጀመሪያ የተገኘው ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ወደ ግዞት ሊከተለው ሲል ‹‹ወደ እስክን ድርያ ሂድ፤ በዚያ የሰማዕትነት አክሊል ይጠብቅሃል፤›› ያለው የኤድኮ ጳጳስ አባ መቃርዮስ ነበር፡፡ ወታደሮቹ ጽሑፎቹን አልፈርምም በማለቱ ከዚያው ደብድበው ገድለውታል፡፡ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነታቸው በመጽናታቸውና የኬልቄዶንን ጉባኤ ባለመቀበላቸው ሠላሳ ሺሕ (30,000) የሚሆኑ ካህናትና ምእመናን ተገድለዋል፡፡ ከጥቂት የሰበካ አብያተ ክርስቲያናት በስተቀር አብዛኞቹ የአብያተ ክርስቲያናት ሕንጻዎች የኬልቄዶንን ጉባኤ ለሚደግፉ ጥቂት ክርስቲያኖች በንጉሠ ነገሥቱ ትእዛዝ እንዲሰጣቸው ተደረገ፡፡

ፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ አምስት ዓመት በግዞት ግፍና ሥቃይ እየተቀበለ ከቆየ በኋላ በ456 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡ መላው የግብጽ ካህናትና ምእመናን የአባታቸውን ማረፍ በሰሙ ጊዜ ታላቅ ሐዘን ተሰማቸው፡፡ ወዲያውኑ ካህናቱና ሕዝበ ክርስቲያኑ ተሰብስበው የዲዮስቆሮስ ዋና ጸሓፊ የነበረውን ጢሞቴዎስ የተባለውን አባት በአንድ ድምፅ መርጠው በዲዮስቆሮስ ፋንታ ዳግማዊ ጢሞቴዎስ ተብሎ የእስክን ድርያ 26ኛው ፓትርያርክ ሆኖ እንዲሾም አደረጉ፡፡ ይህ ምርጫ በሚካሄድበት ጊዜ የንጉሠ ነገሥቱ የመርቅያን ዋና እንደራሴ አገረ ገዥው በእስክንድርያ አልነበረም፡፡ ገዥው ሲመለስ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን አዲስ ፓትርያርክ መርጠው መሾማቸውን በሰማ ጊዜ እጅግ ተናደደ፡፡ አገረገ ዥውም ግብጻውያን ፓትርያርክ የመምረጥ መብት እንዳልነ በራቸው ነገራቸው፡፡ ለማናቸውም እርሱ እስከሚመለስ ድረስ መጠበቅ ነበረባቸው በማለት ምርጫውን እንደማይቀበለው በግልጥ ነገራቸው፡፡ ለእነሱ የተሾመላቸ ውንና መንግሥትም የሚቀበለውን ፕሮቴሪዮስን የግድ መቀበልና ለእርሱ መታዘዝ እንዳለባቸው ነግሮአቸው ሌላ ፓትርያርክ መምረጥ በመንግሥት ላይ እንደማመፅ የሚያስቆጥርና ከባድ ቅጣት የሚያስከትል ነው በማለት አስጠነቀቃቸው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ አዲሱ የእስክንድርያ ፓትርያርክ ዳግማዊ ጢሞቴዎስ ጳጳሳቱን በሙሉ ጠርተው ሲኖዶስ አደረጉና የኬልቄዶንን ጉባኤና የጉባኤውን ደጋፊዎች እንደገና አወገዟ ቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ዲዮኒስዮስ የሚባል አንድ የመንግሥት ወታደራዊ ከፍተኛ ባለሥልጣን ከቊስጥንጥንያ ተልኮ መጣ፡፡ የመጣውም የግብጽ ክርስቲያኖች በሙሉ መንግሥት የሾመውን ፕሮቴሪ ዮስን እንዲቀበሉ ለማድረግ ነበር፡፡ ለእርሱም የማይታዘዙትን ከባድ ቅጣት እንዲቀጣቸው ሥልጣን ተሰጥቶት ነበር የመጣው፡፡ ይህ ባለሥልጣን በመጣ ጊዜ ፓትርያርክ ዳግማዊ ጢሞቴዎስ ከእስክንድርያ ወጥተው የተለያዩ ሀገረ ስብከቶችን በመጐብኘት ላይ ነበሩ፡፡ ፓትርያርኩ በተመለሱ ጊዜ መንበረ ሊቀ ጵጵስናቸው ውጭውም ውስጡም በመንግሥት ቊልፍ ተቈልፎ አገኙት፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑ በዚህ እጅግ ተናደው መንግሥት ወደሾመው ፓትርያርክ ወደ ፕሮቴሪዮስ ሄደው በንጉሡ የተሾመውን ፓትርያርክ ከተደበቀበት አውጥተው ገደሉት፡፡ ይህ ዓመፅ መንግሥትን ስላሳሰበ በሕዝብ ላይ አጸፋዊ እርምጃ ለመውሰድ አልተፈለገም፡፡ ሆኖም ንጉሥ መርቅያን ግብጻውያን የመረጡት ፓትርያርክ ጢሞቴዎስና ወንድሙ ተይዘው ዲዮስቆሮስ ታስሮበት በነበረበት በደሴተ ጋግራ እንዲጋዙ አደረገ፡፡ ይህንም ያደረገው የሕዝቡን መንፈስ ለመስበርና ተስፋ ለማስቈረጥ ነበር፡፡ የሕዝቡ መንፈስ ግን ፈጽሞ አልተለወጠም፡፡

የቊስጥንጥንያ መንግሥት ደጋግሞ ፓትርያርክ ቢልክም ግብጻውያን ግን መንግሥት የሚልካቸውን ፈጽሞ አይቀበሉም ነበር፡፡ እስከ ኬልቄዶን ጉባኤ ድረስ በግብጽ የነበሩ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በቅዳሴና በሌሎች የጸሎት አገልግሎት ጊዜ በግሪክኛ ቋንቋ ነበር የሚጠቀሙት፡፡ ከዚህ በኋላ ግን በቅብጥ ቋንቋ መጠቀም ጀመሩ፡፡ ከ451 ዓ.ም. ጀምሮ ማለት ከኬልቄዶን ጉባዔ በኋላ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ለሁለት ተከፈለች፡፡ በአንድ በኩል የሮም ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ሙሉ ድጋፍ የነበራቸው እኛ መለካውያን ብለን የምንጠራቸው የምዕራቡ አብያተ ክርስቲያናት የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንና የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች የሆኑ ሁሉ ሲሆኑ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የምሥራቅ ወይም የኦርየንታል ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ማለት የግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የሶርያ፣ የአርመንና የሕንድ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው፡፡

የፖፕ ልዮን ቀዳማዊ የሃይማኖት መግለጫ ጦማር

የልዮን የሃይማኖት መግለጫ ጦማር (ደብዳቤ) (The Tome of Leo) የሚከተሉት ነጥቦች ነበሩት፡-

1ኛ/በክርስቶስ ውስጥ የመለኮት ባሕርይና የትስብእት ባሕርይ በአንድ አካል አንድ ሆኑ፤ ያለ መቀላቀል፣ ያለ መለያየትና ያለ መለወጥ፡፡

2ኛ/ እያንዳንዱ ባሕርይ የግብር ክልሉን ጠብቆ ይኖራል፡፡ ይህም ማለት መለኮት የመለኮትን ሥራ ይሠራል፤ ትስብእትም የትስብእትን ሥራ ይሠራል፡፡ 

3ኛ/ ‹‹ከመዋሐድ በፊት ሁለት ነበሩ፤ ከተዋሐዱ በኋላ ግን አንድ ባሕርይ ነው ማለት ሞኝነት ነው፤›› የሚል ኃይለ ቃል ይገኝበታል፡፡

ከልዮን ጦማር ውስጥ ከዚህ በላይ የገለጥናቸው አንድ አካል ከማለቱ በስተቀር የንስጥሮስን ትምህርት ነው የሚገልጡት፡፡ ሁለቱ ባሕርያት አንድ ሆኑ ሲሉ እንደ ኀዳሪና ማኅደር፣ ጽምረትን እንጂ ተዋሕዶን አይገልጡም፡፡ ተዋሕዶ ግን እንደ ነፍስና ሥጋ ነው፡፡ ‹‹እያንዳንዱ ባሕርይ የግብር ክልሉን ጠብቆ ይኖራል›› የሚለው በተዋሕዶ የቃል ገንዘብ ለሥጋ፣ የሥጋ ገንዘብ ለቃል መሆኑንና መገናዘቡን መወራረሱንም የሚጻረር ነው፤ ቅዱስ ቄርሎስ እንዲህ ይላል ‹‹እንቲአሁ ለቃል ኮነ ለሥጋ ወእንቲአሁ ለሥጋ ኮነ ለቃል፡፡›› ይህም ማለት ‹‹የቃል ገንዘብ ለሥጋ ሆነ፤ የሥጋም ገንዘብ ለቃል ሆነ፤›› ማለት ነው፡፡ ይህ ፍጹም ተዋሕዶን የሚያመለክት ነው፡፡ ስለዚህ ነው ሥግው ቃል በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው የምንለው፡፡

የልዮንን ጦማርና የኬልቄዶንን ጉባኤ ውሳኔ በመከተል የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንና የግሪክ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ ‹‹ክርስቶስ ሁለት ባሕርያት አንድ አካል አለው›› ይላሉ፡፡ በአገላለጽም ሁለቱ ባሕርያት የተዋሐዱት ያለ መቀላቀል፣ ያለ መለያየትና ያለ መለወጥ ነው ይላሉ፡፡ አንድ ባሕርይ ለማለት የፈሩት ወደ አውጣኪ ትምህርት ይወስደናል ብለው በመፍራት ነው፡፡ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ሁለቱ ባሕርያት (የሥጋና የመለኮት) ተዋሐዱ ስንል ‹‹ወረሰዮ አሐደ ምስለ መለኮቱ ዘእንበለ ቱስሕት ወኢትድምርት፣ ዘእንበለ ፍልጠት ወኢውላጤ›› (ያለ መቀላቀልና ያለ መጨመር፣ ያለ መለየትና ያለ መለወጥ ከመለኮቱ ጋር አንድ አደረገው፤) እንላለን፡፡ አባቶቻችን ያስተማሯት ርትዕት ሃይማኖታችንም ይህች ናት፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ማስገንዘቢያ

የተወደዳችሁ የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ ተከታታዮች፣ ይህ ጥናታዊ ጽሑፍ ለማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል መቅረቡንና በታኅሣሥ ወር ፳፻፱ ዓ.ም በታተመው ፳፬ኛ ዓመት ቍጥር ፰ ሐመር መጽሔት፣ ከገጽ ፰ – ፲፭ ለንባብ መብቃቱን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡

  NODES
Note 1