ሰፍነጎች በእንስሳት የዘር ግንድ ላይ እጅግ ጥንታዊውንና የታችኛውን ቦታ ይዘው ይገኛሉ።

ስፖንጅ
ሰፍነግ


ልብም ሆነ አንጎል የሌላቸው መሆኑ አይገዳቸውም

ለማስተካከል

ሰፍነጎች ከዕፅዋት ወገን የሚመደቡ ቢመስሉም አርስቶትልና ትልቁ ፕሊኒ በትክክል ከእንስሳት ክፍል መድበዋቸዋል። ሊቃውንት በመላው ዓለም በሚገኙ ውቅያኖሶችና ሐይቆች ቢያንስ 15,000 የሚያክሉ የሰፍነግ ዝርያዎች ይገኛሉ ብለው ይገምታሉ። እነዚህ ሁሉ ሰፍነጎች በቅርጽም ሆነ በቀለም እጅግ የተለያዩ ናቸው። ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል ቀጭን ጣት፣ ጉርድ በርሜል፣ የተዘረጋ ምንጣፍ፣ የሚያምር ማራገቢያና የጠራ ብርሌ የመሰለ መልክ ያላቸው ሰፍነጎች አሉ። አንዳንዶች ከስንዴ ቅንጣት ያነሱ ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ ከሰው የሚበልጥ ቁመት አላቸው። አንዳንድ ሰፍነጎች በመቶ የሚቆጠር ዕድሜ ሊኖራቸው እንደሚችል የሳይንስ ሊቃውንት ያምናሉ።

ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ “ሰፍነጎች በቅርጻቸው፣ በአሠራራቸውም ሆነ በእድገታቸው ከሌሎች እንስሳት የተለዩ ናቸው” ይላል። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? ሰፍነጎች እንደ ሌሎቹ እንስሳት የውስጥ አካል የላቸውም። ታዲያ ልብ፣ አንጎልም ሆነ የነርቭ አውታር ሳይኖራቸው እንዴት በሕይወት መኖር ይችላሉ? በሰፍነግ አካል ውስጥ፣ ለመኖር አስፈላጊ የሆኑ ተግባራትን የሚያከናውኑ ጥቃቅን ህዋሳት ይገኛሉ። የተለየ ተግባር ያላቸው ህዋሳት ምግብ ያጠምዳሉ፣ ምግቦቹን ወደ ሰፍነጉ የተለያዩ የአካል ክፍሎች ያጓጉዛሉ ወይም ቆሻሻ ያስወግዳሉ። ሌሎች ህዋሳት ደግሞ የአጥንት ወይም የውጭ ሽፋን ክፍሎችን በትጋት ይሠራሉ። እንዲያውም አንዳንድ ህዋሳት አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ ወደ ሌላ ዓይነት ህዋስ መቀየር ይችላሉ።

ሰፍነጎች ከሌሎች እንስሳት ልዩ የሚያደርጓቸው ተጨማሪ ባሕርያት አሏቸው። በሕይወት ያለን ሰፍነግ በወንፊት ላይ እየደፈጠጥክ ብትበጣጥሰው ሴሎቹ ዳግመኛ ተሰብስበው የመጀመሪያውን ሰፍነግ ማስገኘት ይችላሉ። ሁለት ሰፍነጎችን አንድ ላይ አድርገህ ብትፈጫቸው ከጊዜ በኋላ ሴሎቹ ተለያይተው የቀድሞዎቹን ሰፍነጎች ይሠራሉ። ናሽናል ጂኦግራፊክ ኒውስ “በዚህ መንገድ ራሱን ከሞት ሊያስነሳ የሚችል አንድም ተክል ወይም እንስሳ የለም” በማለት ተናግሯል።

በተጨማሪም ሰፍነጎች እንደ ሁኔታው በመለዋወጥ መራባት ይችላሉ። አንዳንድ ሰፍነጎች እንደ ሕዋ መንኮራኩር ተስፈንጥረው በመጓዝ በሌሎች አካባቢዎች ሊራቡ የሚችሉ ሴሎችን ይወነጭፋሉ። እነዚህ ሴሎች የሕይወት ተግባሮቻቸውን በሙሉ ለጊዜው አቁመው ረዥም ጉዞ ከተጓዙ በኋላ እንደገና ይነቁና “ከተጫኑበት” ወርደው አዲስ ሰፍነግ ያስገኛሉ። ሌሎች ሰፍነጎች እንደ አስፈላጊነቱ ወንዴና ሴቴ በመሆን በጾታዊ ተራክቦ አማካኝነት አዲስ ሰፍነግ ይወልዳሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ እንቁላል ይጥላሉ።

የባሕር አጽጂዎች

ለማስተካከል

የሥነ እንስሳት ተመራማሪ የሆኑት አለን ኮሊንስ ሰፍነጎች “ከሌሎች እንስሳት የተለየ የአመጋገብ ሥርዓት አላቸው” በማለት ጽፈዋል። ሰፍነጎች በላይኛው ሽፋናቸው ላይ ከሚገኙ ጥቃቅን ቀዳዳዎች አንስቶ በመላው አካላቸው የተዘረጉ በርካታ ቱቦዎችና የተለያዩ ክፍሎች አሏቸው። በእነዚህ ቱቦዎችና ክፍሎች ግድግዳ ላይ ኮአኖሳይትስ የሚባሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጥቃቅን ቀዛፊ ሴሎች አሉ። እያንዳንዱ ሴል ወደፊትና ወደኋላ እንዲቀዝፍ የሚያስችለው አለንጋ መሰል ጫፍ አለው። ቤን ሃርደር የተባሉ ጸሐፊ “[እነዚህ ሴሎች] ውኃ በሰፍነጉ ውስጥ ወደሚገኙ ሌሎች ሴሎች ያለማቋረጥ እንዲፈስ ሲያደርጉ ሌሎቹ ሴሎች ደግሞ በውኃው ውስጥ የሚገኙ የምግብ ቅንጣቶችን ይዘው እንዲዋሃድ ያደርጋሉ” በማለት ገልጸዋል። ሰፍነጎች የሰውነት መጠናቸውን አሥር እጥፍ የሚያህል ውኃ በየሰዓቱ በውስጣቸው እንዲያልፍ በማድረግ በውኃው ውስጥ የሚገኙ ምግቦችን፣ መርዛማ ኬሚካሎችንና እስከ 90 በመቶ የሚደርሱ ባክቴሪያዎችን ውጠው ያስቀራሉ። እንዲያውም የውኃው አፈሳሰስ በሚቀያየርበት ወይም በውስጣቸው የተጠራቀመውን ደለል ማስወገድ በሚፈልጉበት ጊዜ የውኃውን መጠን የመቆጣጠር አሊያም የፍሰቱን አቅጣጫ የመቀየር ችሎታ አላቸው። ዶክተር ጆን ሁፐር “የሰፍነጎችን ያህል . . . ጥሩ የባሕር አጽጂዎች አይገኙም” ብለዋል።

በሰፍነጎች ውስጥ የማያቋርጥ የምግብና የውኃ ፍሰት መኖሩ እንደ ሽሪምፕና ክራብ ላሉት ትናንሽ ፍጥረታት አመቺ መኖሪያ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። በአንድ ሰፍነግ ውስጥ 17,128 የሚያክሉ ነዋሪዎች ተገኝተዋል። በርካታ ባክቴሪያዎች፣ አልጌዎችና ፈንገሶች ከሰፍነጎች ጋር ተረዳድተውና ተደጋግፈው ይኖራሉ። አንድ ሰፍነግ በእርጥብነቱ ከሚኖረው ክብደት ውስጥ እስከ 50 በመቶ የሚሆነውን የሚይዙት ባክቴሪያዎች ናቸው።

ሳይንቲስቶች፣ ሰፍነጎችና ተባባሪ ጥገኞቻቸው የአዳዲስ መድኃኒቶች ምንጭ ሆነው ሊያገለግሉ እንደሚችሉ ተስፋ ያደርጋሉ። እነዚህ መድኃኒቶች ኤድስን፣ ካንሰርን፣ ወባንና ሌሎች በሽታዎችን ለማጥፋት ጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያምናሉ። ሸርሊ ፖምፖኒ የተባሉ ተመራማሪ ይህን በሚመለከት “ተፈጥሮ፣ ኮምፒውተሮቻችን እንኳን ሊያቀናጁ ከሚችሏቸው የበለጡ ውስብስብና ጠቃሚ ሞለኪውሎችን ያመነጫል” ብለዋል።

መስተዋት ዓይነት ነገር የሚፈጥሩበት ሁኔታ

ለማስተካከል

ብዙ ሰፍነጎች ለገላ መታሻ እንደምንጠቀምባቸው ሰፍነጎች ለስላሳ ሳይሆኑ ሻካራ ወይም ጠንካራ ናቸው። እነዚህ ሰፍነጎች ስፔኪዩልስ የሚባሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጥቃቅን የመስታወት ቅንጣቶች አሏቸው። ስፔኪዩሎች በአጉሊ መነጽር ሲታዩ ያላቸው ውበትና ዓይነታቸው የተለያየ መሆኑ በጣም የሚያስገርም ነው። እነዚህ ስፔኪዩሎች በተለያየ መንገድ እንደ ሰንሰለት ሲያያዙ በጣም ውስብስብ የሆነ አጽም፣ የመከላከያ መሣሪያ እንዲያውም ቁመቱ እስከ 3 ሜትር ውፍረቱ ደግሞ እስከ 1 ሴንቲ ሜትር የሚደርስ ገመድ ይፈጥራሉ። አንድ ሥጋ በል ሰፍነግ ፍጥረታትን አድኖ የሚይዝበት ባለ መንጠቆ መረብ አለው።

ጥልቅ በሆነ ባሕር ውስጥ የሚገኘውና የቬነስ አበባ ቅርጫት እየተባለ የሚጠራው የሰፍነግ ዝርያ ስፔኪዩሎችን ተጠቅሞ በጣም ውብ የሆነ የአበባ ጥልፍ መሥራት ይችላል። እነዚህ እንደ ብርሌ የጠሩ የመስታወት ቃጫዎች ለስልክ ማስተላለፊያ የሚያገለግሉትን ዘመናዊ ፋይበር ኦፕቲክ ገመዶች ይመስላሉ። አንድ ሳይንቲስት “እነዚህ ሕያው ቃጫዎች በጣም ጠንካራ ናቸው” ብለዋል። አክለውም “በኃይል ብትቋጥራቸው እንኳ እንደ ሰው ሠራሾቹ ቃጫዎች አይበጠሱም” በማለት ተናግረዋል። እነዚህ ውስብስብ ቃጫዎች በባሕር ውስጥ እንዲሁም ዝቅተኛ የሙቀት መጠን ባለበት አካባቢ እንዴት ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ሳይንቲስቶች በውል ሊረዱት አልቻሉም። የቤል ቤተ ሙከራ ባልደረባ የሆኑት ቼሪ ሙሬይ “በዚህ መንገድ፣ ውስብስብነት የሌለው ይህ ፍጥረት ፋይበር ኦፕቲክ ገመዶችንና እንደ ሴራሚክ ያሉ ነገሮችን በመሥራት ረገድ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት አገልግሏል” ብለዋል።[1]

  1. ^ በአውስትራሊያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ
  NODES
Note 1