ሳምሱ-ዲታና ከ1538 እስከ 1507 ዓክልበ. ('ኡልትራ አጭሩ' አቆጣጠር[1]) ድረስ የባቢሎን ንጉሥ ነበር።

አሚ-ሳዱቃ ልጅና ወራሽ ሲሆን፣ ሳምሱ-ዲታና የባቢሎን (የሃሙራቢ ሥርወ መንግሥት) መጨረሻ ንጉሥ ነበረ። የዘመኑ አመት ስሞች ምንም ዘመቻ ስለማይጠቅሱ ሰላማዊ ዘመን ይመስል ነበር፣ ወደ ደቡቡ ግን የባሕር ምድር ሥርወ መንግሥት ንጉሥ ጉልኪሻር ከሳምሱ-ዲታና ጋር እንደ ታገለ በአንድ ታሪክ ጽላት ተቀረጸ።

በ1507 ዓክልበ. የሐቲ (ኬጥያውያን) ንጉሥ 1 ሙርሲሊ እስከ ባቢሎን ድረስ ዘመተና ከተማውን ዘርፎ አቃጠለው። የኬጥያውያን ሠራዊት የባቢሎን ምስሎች (ጣኦታት) ወደ ሐቲ አገር ወሰዱ፤ ሳምሱ-ዲታናም እንደ ተገደለ ይመስላል።

ይህ የሚታወቀው ከባቢሎን ዜና መዋዕል «በሳምሱ-ዲታና ዘመን፣ ኬጥያውያን ወደ አካድ መጡ» ሲዘገብ፣[2] ደግሞ በኬጥኛ የተለፒኑ ዜና መዋዕል እንደሚለው[3] «እርሱ (ሙርሲሊ) ወደ ሐላብ ሔዶ አጠፋው፤ የሐላብን ምርኮ ወደ ሐቱሻ ወሰደ፤ ከዚያም እስከ ባቢሎን ድረስ ሔዶ አጠፋው፣ ሑራውያንንም አሸነፋቸው፣ የባቢሎንን ምርኮ ወደ ሐቱሻ ወሰደው።»[4]

ባቢሎን በኬጥያውያን ከተዘረፈ በኋላ ኃይሉ እጅግ ስለ ደከመ፣ የኬጥያውያን ጓደኞች ካሳውያንዛግሮስ ተራሮች በቀላሉ ለመውረር ቻሉና አዲስ ካሳዊ ሥርወ መንግሥት መሠረቱ። ካሳውያን የባቢሎን ስም ወደ ካራንዱንያሽ ቀየሩት፤ የባቢሎንም መጀመርያ ካሳዊ ንጉስ 2 አጉም እንደ ነበር ይታመናል። ለዚሁ ዘመን ግን ብዙ ሰነዶች አልተገኙምና «ጨለማ ዘመን» ተብሏል።

የባቢሎን ውድቀት ዓመት መወሰን

ለማስተካከል

ሳምሱ-ዲታና ለ31 ዓመታት የነገሠ ቢታወቅም፣ የባቢሎን (ካርንዱንያሽ) መጀመርያ ካሳውያን ነገሥታት ግን ስንት አመታት ያሕል እንደ ነገሡ በትክክል ስላልተገኘ፣ የባቢሎን ውድቀት አመት በትክክል ለመወሰን ለረጅም ጊዜ አልተቻለም ነበር። ዳሩ ግን በንጉሥ አሚ-ሳዱቃ ዘመን በ8ኛው ዓመት የዘሃራ ሁኔታና አቀማመጥ በደንብ ስለ ተመዘገበ፣ ይህ የታሪክ ሊቃውንት ዘመኑን ለመወሰን ረድቷል። ስለዚሁ የሥነ ፈለክ ቁጠራ፣ የአሚ-ሳዱቃ 8ኛው አመት ወይም በ1702፣ በ1646፣ በ1582፣ ወይም በ1550 ዓክልበ. እንደ ተከሠተ ታወቀ። ዛሬ የብዙ አገራት ታሪክ ሊቃውንት «መካከለኛ አቆጣጠር» የተባለውን ሲቀበሉ፣ የአሚሳዱቃ 8ኛው አመት በ1646 እና የባቢሎን ውድቀት በ1603 ዓክልበ. የሚወስኑት ናቸው። አለዚያ «አጭር አቆጣጠር» ተከትለው የአሚሳዱቃ 8ኛው አመት በ1582፣ የባቢሎንም ውድቀት በ1539 ዓክልበ. ያደርጉታል።

ባለፈው ቅርብ ጊዜ ግን በሥነ ቅርስ እርምጃ ሳቢያ የአሦር ነገሥታት ዘመናት ቁጥር ለማወቅ ስለ ተቻለ፣ የፈረንሳይ ሊቅ ዤራርድ ዠርቱ «ከሁሉ አጭሩ» ('ኡልትራ' ወይም 'አብልጦ አጭር') አቆጣጠር በትክክል እንደሚስማማው አስረድቷል።[5] የአሚሳዱቃ 8ኛው አመት በ1550፣ የባቢሎንም ውድቀት በ1507 ዓክልበ. ሆነ (ወይም ክ.በ. በ1499 እንደ ኤውሮጳውያን አቆጣጠር) ለማለት እንችላለን ማለት ነው።

ቀዳሚው
አሚ-ሳዱቃ
ባቢሎን ንጉሥ
1538-1507 ዓክልበ. ግድም
ተከታይ
2 አጉም

መጣቀሻዎች

ለማስተካከል
  1. ^ https://www.academia.edu/3101613/Chronologie_m%C3%A9sopotamienne_synchronis%C3%A9e(ፈረንሳይኛ)
  2. ^ Benno Landsberger, Assyrische Königsliste und "Dunkles Zeitalter". Journal of Cuneiform Studies 8/2, 1954, 64 (ጀርመንኛ)
  3. ^ 2 BoTU 20 II 10–20 (A), KUB 26, Nr. 74 I 8-11 (B)
  4. ^ Benno Landsberger, Assyrische Königsliste und "Dunkles Zeitalter". Journal of Cuneiform Studies 8/2, 1954, 64 (ጀርመንኛ)
  5. ^ https://www.academia.edu/3101613/Chronologie_m%C3%A9sopotamienne_synchronis%C3%A9e (ፈረንሳይኛ)
  NODES
Note 1