ጌርዮን (ግሪክኛ፦ Γηρυών /ጌሪዎን/) በጥንታዊ ግሪክ አፈ ታሪክ ዘንድ በአትላንቲክ ውቅያኖስ ውስጥ ኤሪጠያ በተባለ ደሴት ላይ የኖረ ታላቅ ተዋጊ ሰው ነበረ። (ይቺ ትንሽ ደሴት በገዲር አጠገብ እንደ ተገኘች፣ በሮሜ ንጉሥ ቫሌንስ ዘመን 356-370 ዓ.ም. በምድር መንቀጥቀጥ በውቅያኖስ እንደ ሰመጠ የሚሉ ታሪኮች አሉ።)

ጌርዮን ፫ ሆኖ ከሄርኩሌስ ጋር ሲዋጋ፣ 550 ዓክልበ. ግድም በጋን ላይ እንደ ተሳለ። ኤሩትዮን ተመትቶ በምድር ተኝቶ ይታያል።

ሄሲዮድ ትውፊቱን ሲጽፈው ጌርዮን ሦስት ራሶችና አንድ ገላ ነበሩት። አይስኩሎስ በጻፈው ትውፊት ግን ሦስት ሰውነቶች ነበሩት። ስቴሲቆሮስ በጻፈው መግለጫ ደግሞ ጌርዮን ፮ እግር፣ ፮ ዕጆችና ፪ ክንፎች ነበሩት። በነዚህ ጽሑፎች ጌርዮን የኢቤሪያ (እስፓንያ) ንጉሥ የቅሪሳውርና የካሊሮዌ ልጅ ይባላል።

በትውፊቱም ባለ ፪ ራስ ውሻ «ኦርጥሮስ» እና ታላቅ የቀይ ከብት መንጋ ነበረው። አንድ እረኛ ኤሩትዮን ደግሞ ነበረው። የተገነነው ተዋጊ ሄርኩሌስ (ወይም ሄራክሌስ) ወደ ኤሪጠያ ሔዶ ከብቶቹን ለመያዝ ግዴታ ደረሰበት። ወደ ደሴቱ ደርሶ መጀመርያ ሄርኩሌስ ውሻውን ኦርጥሮስን በዱላ ገደለው። ከዚያ እረናውን ኤሩትዮንን እንዲህ ገደለው። ጌርዮን ተነሳስቶ ሦስት ጋሻና ሦስት ጦር ይዞ፣ ሦስት ራስ ቁር ለብሶ ሄርኩሌስን እስከ አንጤሞስ ወንዝ አባረረው፣ በዚያ ግን ሄርኩሌስ በመርዛም ፍላጻ ጌርዮንን ገደለው። ከዚያ በኋላ ሄርኩሌስ ቀይ ከብቶቹን ወሰደና ሁላቸውን እስከ ግሪክ አገር ድረስ አመጣቸው። በሮሜ አፈ ታሪክ ግን ሄርኩሌስ ወደ ግሪክ ሲመለስ በጣልያን ሲያልፍ አንዳንዱን ከብት በዚያ ተወ።

ጌርዮን በእስፓንያ አፈ ታሪክ

ለማስተካከል

የእስፓንያ አፈ ታሪክ ስለ ጌርዮን ተጨማሪ ሌላ ዝርዝር አለ። በዚህ መሠረት ጌርዮን ከሊብያ ነው፣ አባቱ የሊብያ ንጉሥ ህያርባስ ነበር። የጌርዮን ሌላ ስም ዴያቡስ ትርጉም በጥንታዊ ሊብያ ቋንቋ «ወርቃማ» ማለት መሆኑ ሲባል፣ ይህ ከሴማዊ ቋንቋዎች (ዳሃብ፣ ዛሃብ ወዘተ.) ጋር ያለው ዝምድና ግልጽ ነው። «ቅሪሳውር» የሚለው ስም በግሪክ «ወርቃማ» ሆኖ ይህ ደግሞ ጌርዮን ወይም ዴያቡስ ማለት ነው ይባላል።

ቱርደታኒያ ንጉሥ ቤቱስ ዘመን፣ የጌርዮን ሠራዊት ከደሴቱ (ኤሪጠያ) ጀምሮ ኢቤርያን በሙሉ ወረረው። በመጨረሻ ቤቱስን አሸንፎ ጌርዮን የኢቤርያ አምባገነን ሆነ፤ በሥሥትና በጭቆና ይገዛቸው ነበር።

በዚህ ዘመን የግብጽ ፈርዖን ኦሲሪስ አፒስጀርመንና በፈረንሳይ ተቀምጦ የማረሻ ጥቅም ያስተምር ነበር። ከዓመታት በኋላ የኢቤርያ ሰዎች አቤቱታ ወደ ኦሲሪስ ስለ ደረሰ፣ ኦሲሪስ ሥራዊት አሠልፎ ወደ ኢቤርያ መጥቶ በታሪፋ በታላቅ ውግያ ጌርዮንን ገደለ። ከዚህ በኋላ የጌርዮን ሦስት ልጆች፣ ሦስቱ «ሎምኒኒ» ለጊዜው የኢቤርያ ገዢዎች ሆኑ። በዚህ የእስፓንያ አፈ ታሪክ፣ የኦሲሪስ ልጅ ሄርኩሌስ ሊቢኩስ የገደላቸው እነዚህ ፫ ሎምኒኒዎች (ወይም «ጌርዮኔስ») ናቸው። ከዚያ ሄርኩሌስ የራሱን ልጅ ሂስፓል በኢቤርያ ዙፋን ላይ አኖረው።

ቀዳሚው
ቤቱስ
የቱርደታኒያ ንጉሥ ተከታይ
ሎምኒኒ
  NODES
Note 1